ዩኒቨርሲቲዉ ከአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ለአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በሀገራዊ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ስልጠና ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 2/2007 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ሀገራዊ ህዳሴና ፈተናዎቹ ፣ሕገ-መንግስታዊ መርሆዎችና ሴኩላሪዝም እንዲሁም ልማታዊ ሲቪል ሰርቪስ የመገንባት ፋይዳና ሀገራዊ ሕዳሴውን በማሳካት ሂደት የሲቪል ሰርቪሱን ሚና አስመልክቶ በተዘጋጁ ሦስት ሰነዶች ላይ በማተኮር የተካሄደ ነው፡፡

የስልጠናው ዓላማ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በተቀላጠፈ መልኩ ማስቀጠልና ሀገሪቱ በምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ዙሪያ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም ለወደፊቱ የሚጠበቁ ስራዎች ምን እንደሆኑ የጠራ ግንዛቤ ማስያዝ ፣ ሀገሪቱ ባለፉት 24 ዓመታት ሰለተጓዘችባቸው ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቶች ለዜጎች ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ማስቻል ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዮሴፍ ኩማ ኢትዮጵያ ከየት ወደየት እየተጓዘች እንደምትገኝ፣ በህዳሴ ጉዞ ፈተናዎች፣ በትምከተኝነት፣ በጠባብነትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለሰልጣኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡ ልማታዊ ሲቪል ሰርቪስ በዩኒቨርሲቲው እንዲጎለብትና ተቋሙ የተሟላ ቁመና እንዲኖረው በማድረግ የደንበኞችን እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ብሎም ሀገራዊ ህዳሴን በሁለንተናዊ መልኩ ማረጋገጥ እንደሚገባም አቶ ዮሴፍ አሳስበዋል፡፡

በህገ-መንግስታዊ መርሆዎችና ሴኩላሪዝም እንዲሁም በአፈፃፀም ሂደት ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ጠለቅ ያለ ዉይይት የተደረገ ሲሆን ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ከሰራተኛ ቅጥር፣ዝውውር፣ ዕድገት፣አገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከሰልጣኞች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዉ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡በቀጣይም በመልካም አስተዳደርና በሌሎች ጉዳዮች በጋራ በመሥራት ለሀገሪቱ ለውጥና ዕድገት ሁሉም ግዴታዉን እንዲወጣ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

በስልጠናው 700 የሚደርሱ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራሮችን ጨምሮ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የመጡ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች የውይይት መድረኮችን መርተዋል፡፡