በዩኒቨርሲቲው በህክምናና ጤና ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በግብርና ኮሌጆች ጥምረት "Hidase International Journal of Science" በሚል ርዕስ የምርምር ሥራዎችን ለማሳተም የሚያስችል አለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናል የምስረታ ጉባኤ ጥቅምት 11/2008 ዓ/ም በዋናው ግቢ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ የምሥረታው ዓላማ የተማሪዎች፣ የመምህራንና የተመራማሪዎች የምርምር ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ማሳተምና ማሳወቅ፣ ለመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ምቹ እድል መፍጠር ብሎም ከምርምር ሥራዎች ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና የሳይንስ ዓለም አቀፍ ጆርናል አስተባባሪ አቶ ሀብቶም ገ/ኪሮስ ገልፀዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን ወ/ሰንበት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዩኒቨርሲቲው ራዕዩን ለማሳካት ከመደበኛው የመማር ማስተር ሥራ ባሻገር ምርምር ላይ ትኩረት በማድረግ አበረታች ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረው የጆርናሉ መቋቋም ይህንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የምርምር ሥራዎች ማህበረሰቡ ዘንድ መድረስ ካልቻሉ ፋይዳቸው አነስተኛ በመሆኑ ይህ ሂደት ውጤት እንዲያመጣና ማህበረሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በተደራጀ መልኩ ዓለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናል በማቋቋም አስፈላጊውን ውጤት ማስመዝገብ ያስፈልጋል፡፡ በዩኒቨርሲቲውም በርካታ የምርምር ሥራዎች በመሠራት ላይ ስለሆኑ በወረቀት ተወስነው እንዳይቀሩና ታትመው ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ የዓለም አቀፍ ጆርናሉ መቋቋም ወሳኝ ነው፡፡     
ከዚህ ቀደም በውሃው ዘርፍ የምርምር ጆርናል ተቋቁሞ በርካታ ስራዎች እየታተሙ ሲሆን በቀጣይም በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ እንዲሁም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች ሦስተኛው ጆርናል እንደሚቋቋም በአውደ ጥናቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ 
በጉባኤው የዓለም አቀፍ ሳይንስ ጆርናል ህትመትን በሚመለከት ሊኖሩ የሚችሉ ቅድመ ሁኔታዎችና መሠረታዊ  እውቀቶች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመድረኩ ከሦስቱ ኮሌጆችና ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች የተወከሉ 50 የሚደርሱ መምህራንና ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን የጆርናሉ መመሥረት በብዙ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውና ለወደፊቱም የምርምር ሥራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለህትመት ለማብቃት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለስኬቱ የበኩላቸውን ሙያዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አረጋግጠዋል፡፡