የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት በካይዘን አመራር ሥርዓት አደረጃጀት ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ አቅርቦ ከአመራር አካላት ጋር ጥር 5/2008 ዓ/ም ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ቁልፍ ተግባራት የተሳኩ እንዲሆኑ ከለውጥ መሣሪያዎች አንዱ የሆነውን የካይዘን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ በተዋረድ ላሉ አካላት ዩኒቨርሲቲው ግንዛቤ የማዳበር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የካይዘን አመራር ፍልስፍና ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው የተሻለ ለውጥ በማምጣት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ፍልስፍናውም ከሁሉም በላይ የአመለካከት ለውጥ ለማስረፅ የሚያስችል እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ እንደገለጹት የካይዘን አመራር ሥርዓት ለተሻለ ለውጥ፣ ጥራትና ምርታማነት የሚያነሳሳና ለተቋማዊ ለውጥ ድርሻው የጎላ ስለሆነ አመራሩንና ሠራተኛውን አሳታፊ በማድረግ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡

የአደረጃጀቱ ዓላማ የካይዘን ባህሪያትን በመረዳት ከፍተኛው አመራር፣ መካከለኛው አመራር እና ፈጻሚው ሠራተኛ በተደራጀና በተቀናጀ መልክ በመንቀሳቀስ በዩኒቨርሲቲው ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ለውጥ ማረጋገጥ መሆኑን የተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳባልቄ ዳልጮ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ ለበላይ አመራሩና በየደረጃው ላሉ ኃላፊዎች ሲሰጥ የነበረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲሁም ሌሎች ተከታታይ ተግባራትን መሰረት በማድረግ የአደረጃጀት ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ለመግባት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

የለውጥ ሥራዎችን በተደራጀ ሁኔታ ለማስኬድ መሰል የስልጠና ሥርዓት መዘርጋቱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው በመጠቆም የአፈፃፀሙንም ውጤታማነት በተገቢው መንገድ ለመገምገም እንዲቻል በአደረጃጀቱ ላይ ጠንካራ ተግባራት ሊሠሩ እንደሚገባ ተሳታፊዎች በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት