OFAB (Open Forum for Agricultural Biotechnology) አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን የSouth Node ማዕከል አድርጎ በመምረጥ የምስረታ አውደ ጥናቱን ጥር 07/2008 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ Click here to see the Pictures.

 

OFAB - በዋናነት ባለድርሻ አካላት እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ ዕውቀትና ልምዳቸውን እንዲጋሩ እና የባዮቴክኖሎጂ ጥቅሞችን ለአፍሪካውያን ለማድረስ የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶችን እንዲያፈላልጉ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ በአፍሪካ እንዲስፋፋና በዚህ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብርም ያደርጋል፡፡ ይህም በኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ምርምር ለማካሄድ፣ ደህንነታቸው የተጠበቁ ምርቶችን ለማምረትና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ከባቢያዊ ሁናቴን በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ይረዳል፡፡

የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዓለማየሁ ኃ/ሚካኤል እንደተናገሩት የSouth Node በደቡብ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያካትት ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የOFAB – Ethiopia  South Node ማዕከል ሆኖ መመረጡ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ የድርጅቱ ዋና ዓላማ በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሠሩ የምርምር ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ ማድረስ፣ ኦፕን ፎረሞችን ማቋቋምና የጋራ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማዕከልነት መመረጡ በዘርፉ ያለውን የምርምር ግኝት ለቅድመ ምረቃና ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ለማድረስ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

የአውደ ጥናቱ አስተባባሪ አቶ ሐብቶም ገ/ኪሮስ ዩኒቨርሲቲው በማዕከልነት የተመረጠበት ምክንያት በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ የባዮቴክኖሎጂ ትምህርት መሰጠቱና የፒ ኤች ዲ መርሃ ግብር ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸው እንዲሁም አካባቢው ለፍራፍሬ ምርት ምቹ መሆኑ ነው፡፡

የSouth Node አመሠራረት፣ በኢትዮጵያ ስላለው የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ትምህርት፣ አለም አቀፋዊ የባዮቴክኖሎጂ ደረጃ ዳሳሳ እና የባዮቴክኖሎጂ ትምህርትና ምርምር በዩኒቨርሲቲው ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩ ሰነዶች በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር እንዳለ ገብሬ፣ በኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ አለሙ እና በሌሎች ምሁራን ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ መሠረት በቅርቡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በOFAB የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ምስረታው እንደሚጠናቀቅና ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ የባዮቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች በዘርፉ ስላለው የግንዘቤ ማነስና ተያያዥ ጉዳዮች ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የባዮቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎች፣ በአካባቢው የሚሠሩ የግብርና ባለሙያዎች፣ ሞዴል አርሶ አደሮችና ከአርባ ምንጭ የግብርና ምርምር ተቋም የተወጣጡ 200 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በኦቾሎ ላንቴ የግብርና ጣቢያ በመገኘት እየተባዙ ያሉትን ምርጥ የሙዝ ዝርያዎች ጎብኝተዋል፡፡

 

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት