የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ባካሄዱት የ2008 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞች፣ ክፍተቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በሠፊው ተዳሰዋል፡፡

በስትራቴጂክ ዕቅድ ት/ግ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ እና በዳይሬክቶሬቱ ባለሙያ አቶ ታምራት ካሳዬ በማብራሪያና በሠንጠረዥ የቀረበው ሪፖርት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይትና ዝርዝር ተግባራትን ለይቶ አሳይቷል፡፡  Click here to see the Pictures.

በግማሽ ዓመቱ ከተከናወኑ የላቁ ተግባራት መካከል በተለያዩ ምክንያቶች በመደበኛው የትምህርት መርሃ-ግብር የመማር ዕድል ያላገኙ ከዩኒቨርሲቲውና ከአካባቢው ማህበረሰብ የተወጣጡ 167 ጎልማሶች በሁለተኛ ዙር የተግባር ተኮር ትምህርት ተከታትለው መመረቃቸው፣ በየትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ሴት ተመራቂዎችን በመምህርነት በመቅጠር የሴቶች ተሳትፎ ማደጉ፣ በጎፋ ሳውላ አዲስ ካምፓስ መከፈቱና የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከልን ተረክቦ በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ መከናወኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

መጽሐፍት፣ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎች አጋዥ ግብዓቶች ተሟልተው የመማር ማስተማር ሂደቱ በወቅቱ የተጀመረ ሲሆን  አዳዲስ ሥርዓተ ትምህርቶችም ተቀርፀው ከትምህርት ሚኒስቴር ህግና ደንብ አንፃር ተፈትሸው ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በእድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅዱ ብሎም በተለያዩ ሀገራዊና ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ተካሂደው የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏል፡፡ ዩኒቨርስቲው ባቋቋማቸው ስድስት የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ልዩ የህግ ድጋፍ ለሚሹ ግለሰቦች ከህግ ምክር እስከ ጥብቅና ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከአካባቢው አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሠፊ የአካባቢ ጥበቃ እና የተፋሰስ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በአንፃሩ የግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅን ተከትሎ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመምህራን ቢሮዎች እና የተማሪዎች ማደሪያ አለመሟላት፣ የማዕቀፍ ግዥ ስርዓት አጠቃላይ ግዢዎችን በማዘግየቱ የግዥና ፋይናንስ ጉዳዮች መጓተትና ለመማር-ማስተማር የሚያገለግሉ ግብዓቶች ላይ ከፍተኛ ዕጥረት መታየት፣ የመምህራን በሚፈለገው ደረጃ በምርምርና  በተጓዳኝ ተግባራት አለመሳተፍ እንደ ችግር የተነሱ ሲሆን የሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተደረገውን ጥረት አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የላቁ ተግባራት እንደተከናወኑ ሁሉ የተወሰኑ የአፈፃፀም ክፍተቶችም የታዩበት በመሆኑ ለቀጣዩ ግማሽ ዓመት ለክፍተቶቹ የላቀ ትኩረት በመስጠት የተሻለ አፈፃፀም ለማሳየት የምንተጋበት ነው ብለዋል፡፡

በዕቅድ አዘገጃጀትና ክለሳ፣ በዕቅድ ክንውን መለኪያዎች እንዲሁም የተሻሉ አፈፃፀሞችን ከማስቀጠልና የሚስተዋሉ ችግሮችን በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት አኳያ የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በግምገማው የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት