አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሜሪከን ሀገር ከሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ/Cornel University/፣ ከዓለም የምግብ ድርጅት/FAO/ እና ITOCA (Information Training and Outreach Centre for Africa) ጋር በመተባበር ከየካቲት 21-22/2008 ዓ/ም ለሁለት ቀናት የTEEAL-AGORA እና Information Skill Training የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ Click here to see the Pictures.

የሥልጠናው ዓላማ በተለይም ግብርና እና ተያያዥ ሙያዎች ላላቸው ተመራማሪዎች፣ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎችና ሠራተኞች የTEEAL/ The Essential Electronic Agricultural Library/  እና AGORA/ Access to Global Online Research in Agriculture/ ፕሮግራሞችን በማስተዋወቅ ሌሎችን እንዲያሰለጥኑ እና በአጠቃቀም ወቅት እገዛ እንዲያደርጉ  ማስቻል መሆኑን የቤተ-መጽሐፍትና መረጃ አገግልሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አልአዛር ባህሩ ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የ TEEAL ዳታቤዝ ከተገጠመ ረዥም ጊዜን ያስቆጠረ ቢሆንም በአግባቡ አገልግሎት ላይ አልዋለም፡፡ ፕሮግራሙ ለመማር ማስተማርም ሆነ ለጥናትና ምርምር በተለይም የድህረ ምረቃ ትምህርትን ለማስፋፋት ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ በሠፊው መተዋወቅ ስለሚገባው ይህ ሥልጠና ተዘጋጅቷል፡፡

በ ITOCA Training and Outreach Officer አቶ ነፃነት አንሙት ‹TEEAL› በግብርና እና ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የምርምር ጆርናሎች ዲጂታል ስብስብ ሲሆን ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎችና የላይብረሪ ባለሙያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የምርምር ጽሁፎችን ያለ ኢንተርኔት ግንኙነት ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የኤሌክትሮኒክ ላይብረሪ ምንነትና ይዘት፣ አራቱ የ research4life ፕሮግራሞች፦ ARDI፣ AGORA፣ HINARI እና OARE፣ የ TEEAL ዳታቤዝ፣ መሠረታዊና ውስብስብ የፍለጋ ዘዴዎች /basic and advanced search/ እንዲሁም reference management የሚሉ ርዕሶች ተዳሰዋል፡፡

ITOCA በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የቤተ-መጽሐፍት ባለሙያዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ የመረጃ ባለሙዎች እና ተማሪዎችን የመረጃ መረብ ቴክኖሎጂ እውቀት ማሳደግን ዓላማ አድርጎ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን TEEAL፣ AGORA፣ HINARI እና OARE ፕሮግራሞችን ለማስተዋወቅ መጠነ ሰፊ እገዛዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቢል እና ሚሌንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት የአፍሪካ ሀገራት መሠል ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው፡፡

በሥልጠናው ከጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት፣ ከሚቲዎሮሎጂና ባዮሎጂ የትምህርት ክፍሎች፣ ከግብርና ኮሌጅ ከሁሉም የትምህርት ክፍሎች፣ ከቤተ-መጽሐፍት እና ከመረጃና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የተወጣጡ ባለሙያዎች እንዲሁም የሁሉም ኮሌጆች የምርምር አስተባባሪዎች ተሣትፈዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት