በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ግጭቶችን አስመልክቶ በዩኒቨርሲቲውና በ STRONGBOW ፕሮጀክት ትብብር ‹‹Cross Regional Boundary Resource Use Conflicts: The Case of Nech Sar National Park›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የጥናት ፕሮፖዛል ላይ ጥር 16/2008 ዓ.ም የባለድርሻ አካላት አውደጥናት ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና የፕሮጀክቱ ተመራማሪ አቶ ልዑልሰገድ በላይነህ እንደገለጹት የአውደጥናቱ ዓላማ በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ለሚስተዋሉ ችግሮች  ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመፈለግ ለሚሠራው ጥናታዊ ጽሑፍ ግብዓት ማሰባሰብ ነው፡፡

በውይይቱ እንደተመለከተው ልቅ ግጦሽ፣ ህገ-ወጥ ሰፈራ፣ የእርሻ መስፋፋት፣ ሀይቆች ላይ ህገ-ወጥ አሳ ማስገር፣ ለማገዶና ለግንባታ ሥራዎች ደን ጭፍጨፋ፣ ህገ-ወጥ አደን እንዲሁም በቤት እንስሳት አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎች ወደ ዱር እንስሳቱ መተላለፍ በፓርኩ ህልውና ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይህም በየዓመቱ ከ10-15 በመቶ እያደገ የመጣውን የቱሪስት ፍሰት የሚያስተጓጉል፣ ለከፍተኛ የአየር መዛባት የሚዳርግ እና ሀገሪቱ ብሎም ህብረተሰቡ ከፓርኩ የሚያገኙትን ጥቅም የሚያስቀር ነው፡፡

የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርዬ ፓርኩ ሲመሠረት ከፍተኛ ጥናትና ጥንቃቄ የተደረገበት ቢሆንም ከምሥረታው በኋላ አዋጅና ሥርዓተ አያያዝ ባለመደንገጉ ለዓመታት የዘለቁ ችግሮችን አስከትሏል ብለዋል፡፡ በፓርኩ ዓለም ዓቀፍ ህጎች እንዳይተገበሩ እንቅፋት የፈጠረ በመሆኑ የፓርኩን ሀገራዊ ጠቀሜታ በማሰብ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሔ ማፈላለግ ይገባቸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ሊካሔድ የታሰበው ጥናትም የመፍትሔው አንድ አካል የሚሆን ነው፡፡

ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የኦሮሚያ እና የደቡብ ክልሎችን የሚያዋስን በመሆኑ የሁለቱም ክልሎች ባለድርሻ አካላትና የፓርኩ አመራር አካላት በዓውደ ጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡