ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ከማህበራዊ ሳይንስና ሰነ ሰብ ኮሌጆችና ከህግ ትምህርት ቤት በ2008 የትምህርት ዘመን በአንደኛው ሴሚስቴር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች መጋቢት 23/2008 ዓ/ም የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በኮሌጆቹና በትምህርት ቤቱ አዘጋጅነት የተካሄደው ፕሮግራም ዓላማ በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና በመስጠት ማበረታታትና ሌሎች ተማሪዎች ተሞክሮ የሚወስዱበት ማነቃቂያ መድረክ መፍጠር ነው፡፡


የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይና ልዩ ረዳት አቶ አብዮት ጸጋዬ የተመዘገበው አመርቂ ውጤት የመምህራኑና የተማሪዎቹ የጋራ ጥረት ሲሆን ቀጣይነት እንዲኖረው መሰል የማበረታቻ ፕሮግራሞች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ብቁና ውጤታማ ሆኖ ሀገርን ለማገልገል ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በስነ-ምግባር መታነፅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡


የማህበራዊ ሳይንስና ሰነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ተሾመ ይርጉ መጠነ ማቋረጥን አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት በ2008 የትምህርት ዘመን በኮሌጁ አንደኛና ሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች መካከለኛ መጠነ ማቋረጥ ቢኖርም በሶስተኛና በመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች ዜሮ የመጠነ ማቋረጥ ስኬት ተመዝግቧል፡፡ በ2007 የትምህርት ዘመን በተመሳሳይ ሴሚስቴር በኮሌጁ በአንደኛና በሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች በአጠቃላይ 8.3 በመቶ የነበረው መጠነ ማቋረጥ ወደ 5.7 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን በቀጣይም ዜሮ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡


የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ወንድወሰን ጀረኔ እንደገለፁት በኮሌጁ በአንደኛ ሴሚስቴር ከ3,936 ተማሪዎች መካከል 5.5 በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸው መሻሻል ያለበት ክፍተት ነው፡፡ መጠነ ማቋረጥና መጠነ መውደቅን ለመቀነስ በቴክኖሎጂና ትምህርት ልማት ሠራዊት ዕቅድ መመራት፣ የመምህራንና ተማሪዎችን ጥረት አስተባብሮ መስራት እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም ደካማ የሆኑ ተማሪዎችን ማገዝ ያስፈልጋል፡፡


የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ከመማር ማስተማር ሥራ በተጨማሪ ተማሪዎቹን አፍሪካ አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ በማሳተፍ እውቅና አስገኝቷል ብለዋል፡፡ ት/ቤቱ መምህራንና ተማሪዎችን ያሳተፈ ነጻ የህግ ድጋፍ ለማህበረሰቡ ተደራሽ አድርጓል፤ ብሔራዊ የህግ ተማሪዎች የመውጪያ ፈተናንም በስኬት አጠናቋል፡፡


ዩኒቨርሲቲው መጠነ ማቋረጥና መጠነ መውደቅን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የመጠነ መመረቅ ምጣኔን ለማሳደግ ከወትሮው በበለጠ ትጋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ከሁለቱ ኮሌጆችና ከህግ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ መጨረሻ ዓመት በሁለቱም ጾታዎች በሴሚስቴሩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ከኮሌጅ ዲኖችና ከዕለቱ እንግዳ እጅ ሽልማታቸውን ተረክበዋል፡፡ የማበረታቻ ሽልማቱ እንዳስደሰታቸው እንዲሁም በይበልጥ ለመስራትና ሌሎች ተማሪዎችን ለመርዳት ያነሳሳቸው መሆኑን ተሸላሚዎቹ በአስተያየታቸው  ገልጸዋል፡፡