በ2008 የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲውን ለተቀላቀሉ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎችና በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ ሴት ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ስልጠና ከመጋቢት 3-4/2008 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ Click here to see the Picture.

በስልጠናው የመማር ክህሎት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የድካም ስሜትን መቆጣጠሪያ መንገዶች፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እና የሥነ ተዋልዶ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ስልጠናው ሴት ተማሪዎች የጾታ ትንኮሳን የመከላከል አቅማቸው እንዲያድግ፣ በራስ የመተማመን ብቃታቸው እንዲጎለብት፣ የማህበረሰቡን የአመለካከት ችግሮችና በመማር ማስተማር ሂደት የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በትምህርት ቆይታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እና ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ያደርጋል ያሉት የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የስርዓት ጾታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ታደለ ሸዋ ናቸው፡፡

በትምህርት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከመምህራንና ከስርዓተ ጾታ ባለሙያዎች ጋር ግልጽና በቂ ውይይት በማድረግ እንዲሁም የምክር አገልግሎት በማግኘት  የአቻ ግፊቶችን በጠንካራ ስነ ልቦና መቋቋም እንደሚቻል በስልጠናው ተገልጿል፡፡

ስልጠናው በማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህራንና በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጤና ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን 150 ሴት የዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን ጨምሮ ከአባያና ከፊውቸር ሆፕ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች 30 በድምሩ 180 ሴት ተማሪዎችን አሳትፏል፡፡

በስልጠናው መካፈላቸው በራስ የመተማመን ብቃትና የጾታ ትንኮሳ መከላከያ መንገዶችን በጥልቀት እንዲያውቁ ያደረጋቸው መሆኑን የገለጹት ሰልጣኞች በሴትነታቸው የሚደርስባቸውን መሰናክሎች ተቋቁመው ውጤታማ በመሆን ዓላማቸውን እንደሚያሳኩም ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በሁለት ቡድኖች በአባያ እና ነጭ ሣር ካምፓሶች ተሰጥቷል፡፡