የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባባሪያ ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በመሰረታዊ የሂሳብ መዝገብ አያያዝና በግብር ህጎች ዙሪያ ለከተማው ግብር ከፋይ ነጋዴዎች የካቲት 26/2008 ዓ/ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አሸናፊ ናና እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ ግብር ለሀገር ልማትና ለህዝብ እድገት ያለውን ፋይዳ ማሳየት፣ በግብር ህጎች ላይ ግንዛቤ መፍጠርና የግብር ከፋዮች ተነሳሽነትን በማጎልበት የመንግስትን ግብር በፈቃደኝነት እንዲከፍሉ ማስቻል ነው፡፡

ሥልጠናው መሰረታዊ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣ የግብር ህጎች በኢትዮጵያ፣ የግብር ህግ ጥሰቶች ወይም የግብር ወንጀል ዓይነቶችና አስተዳደራዊ ቅጣቶች የሚሉ ርዕሶችን አካቷል፡፡ በግንዛቤ ጉድለትና የግብር ህግ ክፍተቶችን በመጠቀም የሚፈጠሩ የግብር ክልከላ፣ ማዘግየት፣ ማጭበርበርና መሰል የግብር ወንጀሎች በስፋት ተብራርተዋል፡፡

ለግብር ከፋዩ ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች አለመፈጠር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ደረሰኝ ክትትልና ቁጥጥርን አቅዶ አለመስራት፣ ሸማቹ ህብረተሰብ ለገዛው ዕቃ ደረሰኝ የመቀበል ባህል አለማዳበርና ግብር ከፋዮች ለመንግስትና ለሀገር ታማኝ ሆነው ለገዥው ደረሰኝ ያለመስጠት ችግሮች በውይይቱ ተነስተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ታደሰ ግብር በአግባቡ ተሰብስቦ ለህዝብ ጥቅም ሲውል በመሠረተ ልማት ግንባታና ማስፋፊያ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን በርካታ የልማት ዕቅዶችን በማስፈፀም ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ከሚያከናውናቸው በርካታ የልማት ሥራዎች በተጓዳኝ የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ በእውቀት ለማዘመን ስልጠና ማዘጋጀቱ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡

የታክስ ሥርዓት የማህበራዊ አገልግሎቶችና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች ዕቅድ ማስፈጸሚያ መሳሪያ መሆኑን የአርባ ምንጭ ከተማ ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አፈወርቅ አለማየሁ ገልፀዋል፡፡ አርባ ምንጭ ከተማ ከክልሉ ደረጃ ሁለት ከተሞች አንዷና ከመንግስት በጀት ድጎማ ውጪ በራስ ገቢ የምትተዳደር ብትሆንም በ2008 በጀት ዓመት ከግብር ከፋዮች ለማሰባሰብ ከተያዘው ዕቅድ የተፈፀመው ከግማሽ በታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የዲን ተወካይ አቶ ሄኖክ በቀለ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግብር አከፋፈል ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል የግብር ከፋዩን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎች ወረዳዎች በመንቀሳቀስ መሰል ስልጠና ይሠጣል ብለዋል፡፡

በስልጠናው በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ የደረጃ ሀ (ዓመታዊ ሽያጭ ከ500 ሺ ብር በላይ)፣ ደረጃ ለ (ዓመታዊ ሽያጭ ከ101 - 500 ሺህ ብር) እና ደረጃ ሐ (ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ ኢንተርፕራይዞች የተሸጋገሩ ዓመታዊ ሽያጭ 500 ሺ ብር) ግብር ከፋዮች ተሳትፈዋል፡፡