የዩኒቨርሲቲውን የልማታዊ መልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዕቅድ አስመልክቶ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕ/ጽ/ቤት በሥሩ ከሚገኙ የሥራ ክፍሎች ከተወጣጡ ሠራተኞች ጋር የካቲት 16/2008 ዓ/ም የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የልማታዊ መልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዕቅድ ዓላማ በዩኒቨርሲቲው በተገነባ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት፣ የመፍቻ ስልት በማውጣትና በመተግበር ለሁሉም ተገልጋዮች ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን የደንበኞችን በተለይም የተማሪዎችን ፍላጎት ማርካት መሆኑን የቀረበው ሰነድ ያስረዳል። በዚህም መልካም አስተዳደርን በማስፈን የተገልጋይ እርካታን 85 በመቶ ማሳደግ የዕቅዱ ግብ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቁ ዜጋን ለማፍራት በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና በዕቅዱ መሠረት በመተግበር የተጠቃሚውን እርካታ የሚያሳድግ ሥርዓት እንደሚዘረጋ የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ተናግረዋል፡፡

የደረጃ እድገት፣ የቅጥር አፈፃፀም፣ የሰራተኛ ማህደር አያያዝ፣ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ተገቢነት፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አሰራር ሥርዓት አግባብነት፣ የትጉ ሰራተኞች እውቅና አሰጣጥ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የደንብ ልብስ አሰጣጥ፣ የሥራ ሰዓት አጠቃቀም እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በውይይቱ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተወያዮቹ ጥያቄዎቻቸውን ለበላይ አመራሩ ያቀረቡ ሲሆን የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ የይዞታ ልማት፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር፣ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር፣ የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር፣ የጠቅላላ አገልግሎትና የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬቶች ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች፣ የፀጥታና ደህንነት ጽ/ቤት አስተባባሪዎች  እንዲሁም የየካምፓሱ አስተዳደር አካላት ተገኝተዋል፡፡