በቤልጂዬም VLIR-OUS አማካኝት ላለፉት አራት አመታት በነጭ-ሣር ብሔራዊ ፓርክ እና አባያና ጫሞ ሀይቆች ህልውና ላይ በማተኮር ሲከናወን የቆየውን ፕሮጀክት መጠናቀቅ አስመልክቶ በዩኒቨርሲቲው መጋቢት 26/2008 ዓ/ም የማጠቃለያ አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ፕሮጀክቱ በዋናነት ዩኒቨርሲቲውን በትምህርት፣ ስልጠናና ልማት ዘርፎች በማገዝ ባለሙያዎችን ለማብቃት እንዲሁም በፓርኩና በሐይቆቹ ላይ የተጋረጡ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በማጥናት ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማበጀት በማለም እ.ኤ.አ በ2012 የጋራ ስምምነት አድርጓል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ለዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል ልማት መጎልበትና ውጤታማ የጥናትና ምርምር ሥራ  ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ባመቻቸው እድል የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በቤልጀዬም ሀገር የተከታተሉት የዩኒቨርሲቲው መምህራን ዶ/ር ስሞኦን ሽብሩና ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በአውደጥናቱ የምርምር ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ስሞኦን ሽብሩ “Response of Vegetation, Small Mammals and Large Herbivores to Human Induced Pressures in Savanna Plains of Nech-Sar National Park” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጹሁፋቸው በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የሰው ልጆች አሉታዊ ተፅዕኖ በእጽዋት እና በአጥቢ እንስሳት ላይ ያመጣውን ጫና በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ዳሰዋል፡፡ ከፓርኩ ሥነ-ምህዳር በሂደት መጎሳቆል ጋር ተያይዞ በውስጡ የሚገኙ እንስሳት ቁጥር መቀነስ ፣ የብርቅዬ እንስሳት የመጥፋት ስጋት፣ የመሬት ሽፋን ለውጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ጥናቱ በጥልቀት ተመልክቷል፡፡

በዶ/ር ፋሲል እሸቱ “The Ecology of Major Ethiopian Rift valley Lakes: Abaya and Chamo with Special Reference with Food Web Structure and Water Quality” በሚል ርዕስ የቀረበው የጥናት ጽሁፍ በአባያና ጫሞ ሀይቆች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ጥናቱ በተለይም በጫሞ ሀይቅ ላይ አንኳር የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ የማውጣት ዓላማ ያለው ሲሆን የችግሮቹ ዋነኛ ምንጭ የሆኑት የጎርፍ ውኃ መስረግና የደን መመናመን ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ጥናቱ እንደሚጠቁመው በቱሪስት መስህብነት፣ በዓሳዎች ህልውና እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አደጋ በመጋረጡ የከፋ ነገር እንዳይከሰት ከወዲሁ ጥበቃ ሊደረግ ይገባል፡፡

በጥናታዊ ጽሁፎቹ መነሻነት ፓርኩንና በዙሪያው ያለውን አካባቢ በተመለከተ ፓሊሲ ስለማዘጋጀት፣ ስለፓርኩ ክልል ፖለቲካዊ ጉዳይ፣ የእጽዋት መመናመንን ለመቅረፍ መወሰድ ስላለበት እርምጃ፣ ስለ ማህበረሰቡ ተጽዕኖ እና መሰል ጉዳዮች በተሳታፊዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በተመራማሪዎች የቀረቡት የጥናት ውጤቶች ለፓሊሲ አውጭዎችና በቀጣይ በአካባቢው ጥናት ለሚያደርጉ አካላት ትልቅ የመረጃ ምንጭ በመሆን የሚያገለግል ነው፡፡

በፕሮግራሙ ፕሮጀክቱን የሚደግፉ ከቤልጅዬም የመጡ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎችን ጨምሮ ከ120 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡