ሰላም ፎረም ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር ለፎረሙ አመራርና ባለድርሻ አካላት የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽን አስመልክቶ ከመጋቢት 21-22/2008 ዓ/ም የግንዛቤ ማዳበሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግጭት መከላከልና መፍታት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ወ/ሚካኤል እንደተናገሩት ቀላል ክስተቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ መረጃ በመስጠትና በመከላከል ረገድ ፎረሙ የጎላ ሚና ያለው በመሆኑ ይህንን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ስለሆነም ስልጠናው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበትን ግንዛቤ ያስጨብጣል ብለዋል፡፡

በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ የክልሉ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ፎረምና የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ የመረጃ አስተባባሪ አቶ ኃይሉ ማቲዎስ ባቀረቡት ሰነድ እንደተመለከተው ግጭቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ጉዳዮችን መሰረት አድርገው ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ሲሆን የግጭት አመላካቾችን ለይቶ አለመረዳት ለተሳሳተ ውሳኔና ጉዳት ይዳርጋል፡፡ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ስርዓት የግጭቶችን አጠቃላይ አዝማሚያ ለመከታተል፣ የወደፊት አዝማሚያን ለመተንበይ፣ ለተጠቃሚዎች መረጃን በማሰራጨት ግንዛቤን ለማስፋፋትና የግጭትን አሉታዊ አቅጣጫ ለማስቀየር እንዲሁም ብጥብጥን ለመከላከል ያስችላል፡፡

የሰላም ምንነት፣ አስፈላጊነትና አመለካከቶች፣ የግጭት ምንነት፣ አፈታትና መከላከል እንዲሁም የፈጣን ምላሽ ዓይነቶች በስልጠናው ተዳሰዋል፡፡ ሰላም ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ ሠልጣኞች ያገኙትን የቅድመ ማስጠንቀቂያና የሰላም እሴት ግንባታ ዕውቀት ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በማድረስ የግቢው ሰላም እንዲጠበቅና አሁን ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲረባረቡና የሰላም አምባሳደር ሆነው እንዲንቀሳቀሱ አስተባባሪው አሳስበዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱ በተገቢውና በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፎረሙ ተማሪዎችን በማሳተፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን አስቀድሞ በመፍታት ረገድም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጠንካራ ተሳትፎውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ በተደጋጋሚ ስልጠናዎችን በመስጠትና መረጃዎችን በመለዋወጥ ችግሮች ከመባባሳቸው በፊት እልባት እንዲያገኙ ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው የተነሱ ጉዳዮች ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ ከማህበረሰቡ ጋር በመግባባት ችግሮችን ለመቅረፍና ሰላምን ለማዳበር መከተል ያለባቸውን አቅጣጫ እንዳስገነዘባቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ሆነ ውጪ በሚኖራቸው ቆይታ ለሰላም የቆመ ዜጋን ለማፍራት በትጋት እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠላም ፎረም  የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ በመሆናቸው ባህልና እሴቶቻቸውን የሚለዋወጡበት ስርዓት ማዳበር፣ ችግሮችን በግልፅ ተነጋግሮ መፍታት የሚችል ማህበረሰብ መፍጠርና የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ማበርከትን ዓላማ አድርጎ ተመሥርቷል፡፡