የ2008 ዓ/ም የአንደኛ ሴሚስቴር የስራ አፈፃፀምና የተማሪዎች ውጤትን አስመልክቶ ከመምህራን፣ ከትምህርት ክፍሎችና ከኮሌጅ ዲኖች ጋር መጋቢት 15/2008 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የውይይቱ ዓላማ የአንደኛው መንፈቀ ዓመት የመማር ማስተማር ስራ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመገባቱ በፊት በየትምህርት ክፍሉ የነበረውን አፈፃፀም ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲሁም የተማሪዎችን ውጤት መገምገምና ለቀጣይ ሴሚስቴር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን መለየት ነው፡፡

በአንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ከፍተኛ ውጤቶች መመዝገባቸው፣ የክፍለ ጊዜ አጠቃቀምና መ/ራን እራሳቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት የታዩ ጠንካራ ጎኖች ናቸው፡፡ በተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶች የ FX መብዛት፣ በአንዳንድ መ/ራን በኩል የተማሪዎችን ውጤት በወቅቱ አለማስገባት፣ በየምዕራፉ ወቅቱን የጠበቁ ሙከራዎችን አለመስጠት እንዲሁም  በተማሪዎች በኩል ሁሉንም የትምህርት ዓይነት በእኩል አይን ማየት አለመቻልና ኩረጃ የመሳሰሉት ሊሻሻሉ የሚገባቸው ተብለው በውይይቱ ላይ ተነስተዋል፡፡

መጠነ ማቋረጥና መጠነ መውደቅን ከ5% በታች ማድረስ በዩኒቨርሲቲው ዓመታዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን በኮሌጆችና በትምህርት ክፍሎች ቢለያይም አበረታች ውጤት መገኘቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ መምህራን ተከታታይ ምዘናና የማጠናከሪያ ትምህርት ቢሰጡ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚረዳ ሲሆን የትምህርት ክፍሎችም መምህራኑ የመማር ማስተማር መርሆዎችን ተከትለው መሥራታቸውን በመረጃ ተደግፈው ጠንካራ ክትትል ማድረግና በአግባቡ በማይሠሩት ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ተማሪዎች በትምህርት አይነቶች መካከል ልዩነት እንዳያሳድሩና አሳንሰው የሚያዩት ኮርስ እንዳይኖር መምህራን በትምህርት አሰጣጥ፣ በጊዜ አጠቃቀም፣ የትምህርቱን ዓላማ ለማስገንዘብ በሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም በተማሪ አያያዝ  ትልቁን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች አነስተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በመሆናቸው የተጨማሪ ማጣቀሻ መፅሃፍቶች ውሰት፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና መሰል ድጋፎች ቢደረግላቸው ችግሩን ለማስወገድ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተሳታፊዎቹ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የፈተና ኩረጃ ባህልን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራበት አሳስበዋል፡፡