ዩኒቨርሲቲው ከVLIR-OUS ቤልጂየም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የ4 ዓመት የእንሰት ቲም ፕሮጀክት መጋቢት 26/2008 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በቤልጂየም የፕሮጀክት ቡድኑ አባልና አንቀሳቃሽ ፕሮፌሰር ካሬን ቫንካምፐንሀውት /prof. Karen Vancampenhout የእንሰት ተክልን አስመልክቶ ሲናገሩ የእንሰት ተክል ድርቅን የመቋቋም አቅሙ የላቀ ሲሆን 15 ሚሊየን ያህል የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ህዝብ እንሰትን ለምግብነት ይጠቀማል ብለዋል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል፡፡

ፕሮጀክቱ የእንሰት ንጥረ ነገር ይዘትና የገበያ ትሥሥሩን በድህረ ምርት መሰብሰብ ቴክኒኮች ማሻሻል እንዲሁም በጋራ የምርምር ውጤቶች የሚገኙ የተሻሻሉ ዘዴዎችን በማላመድ ባላድርሻዎችን የማሳተፍና ተጠቃሚ የማድረግ  ዓላማ ያለው ሲሆን ስነ-ምህዳራዊና አስተዳዳራዊ ጉዳዮች በእንሰት ምርት ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖም ይፈትሻል፡፡

በጋሞ ከፍተኛ ቦታዎች ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ከዩኒቨርሲቲው ለሁለት የፒኤችዲ ምሁራን አቶ ሳቡራ ሻራ እና አቶ አዲሱ ፈቃዱ የትምህርት ዕድል የሰጠ ሲሆን የግብርና ስነ-ምህዳርና ምርታማነትን በማጥናት የእንሰት ምርትን ማሻሻል ለእንሰት በሽታዎች መፍትሄ ያፈላልጋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሌላኛው ቤልጂየማዊ ረዳት አስተባባሪ ዶ/ር ሴፔ ዴከርስ እንደተናገሩት እንሰት በኢትዮጵያ ከ2500 ዓመታት በፊት ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ያለ ተክል ነው፡፡ እንሰት ከፍተኛ የካርቦሀይድሬት ክምችት ያለው፣ ድርቅን መቋቋም የሚችል፣ ወቅት ሳይጠብቅ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ረሃብን ለመቋቋም እንዲሁም በደጋማ አካባቢዎች በጎርፍ የሚሸረሸረውን አፈር ለመከላከል የሚረዳ ዓይነተኛ ተክል ነው፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የእንሰት ፕሮጀክት ቡድን አባል ዶ/ር ፋንታሁን ወ/ሰንበት ዩኒቨርሲቲው ከቤልጂየም አጋሮቹ ጋር በጋራ በቀረፀው ፕሮጀክት ለእንሰት ተክል የሚገባውን ትኩረት ለመስጠትና ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ በማከናወን ላይ ነው፡፡ በቀጣይም ደረጃውን የጠበቀ በእንሰት አዘገጃጀት ሂደትና በእንሰት አጠውላጊ በሽታ /ባክቴሪያል ዊልት/ ላይ የሚሠራ ቤተ-ሙከራ ይደራጃል ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ በጋሞ ከፍተኛ አካባቢዎች የእንሰት ምርት ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ፕሮፖዛሎች ቀርበዋል፡፡ በፒኤችዲ ምሁር አቶ ሳቡራ ሻራ የቀረበው በእንሰት አጠውላጊ የባክቴሪያ ዋግ /ባክቴሪያ ዊልት/ ላይ ያተኮረ የጥናት ፕሮፖዛል እንደሚያሳየው የእንሰት አጠውላጊ በሽታ በሁሉም የግብርና ስነ-ምህዳሮች ላይ የሚገኝ፣ ሁሉንም የእንሰት ደረጃዎች የሚያጠቃና የእንሰት ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ያለ በሽታ ነው፡፡ አብዛኛው የጋሞ ከፍተኛ አካባቢ እንሰት አምራች ከሚባሉት ውስጥ በዋናነት የሚመደብና ከ17 ሺ ሄክታር በላይ እንሰት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 11ሺ ሄክታር ያህሉ መሬት በእንሰት የተሸፈነ ነው፡፡ የእንሰት ምርት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የተሻሻሉና በሽታ የሚቋቋሙ ዝርያዎችን መጠቀም የተሻለ መፍትሄ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በፒኤችዲ ምሁር  አቶ አዲሱ ፈቃዱ የቀረበው የምርምር ፕሮፖዛል የቆጮን ጥራት ለማሻሻል የማብላላት ሂደቱን አሳጥሮ  እንሰቱ ተፍቆ ለምግብነት እስከሚውል ከ2 እስከ 3 ወር የሚፈጀውን በአንድና በሁለት ሳምንት እንዲደርስ የማድረግ ዘዴ ላይ ያተኩራል፡፡ ቆጮ የቆይታ ጊዜው ባጠረ መጠን የምግብነት ይዘቱ እንደሚጨምር፣ መልኩ እንደሚነጣና ጠረኑም እንደሚሻሻል በሙከራ በመረጋገጡ ይህንን በቴክኖሎጂ አስደግፎ በሰፊው ለመተግበር የጥናት ፕሮፖዛሉ መዘጋጀቱን አቶ አዲሱ ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የቤልጂየም ካቶሊክ ክላስተር ዩኒቨርሲቲ ኤክስፐርቶችና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቡድኖች የሚሳተፉበት ሲሆን  300,000 ዩሮ ተመድቦለታል፡፡ ፐሮፌሰር ካሬን በቤልጂየም የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ሲሆኑ የቀድሞው የአ/ም/ዩ ፕሬዝደንትና የአሁኑ የኢትዮጵያ የብዝሃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በሀገር ውስጥ ያስተባብራሉ፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን በመጀመሪያው ደረጃ በሁለት ዓመታት ውስጥ ችግሮችን የመለየት ሥራ ይጠናቀቃል፡፡ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃዎች አንድ አንድ ዓመት ጊዜ ያላቸው ሲሆኑ በታዩ ችግሮች ዙሪያ ከቅድመ እና ድህረ ምርት መሰብሰብ እንዲሁም ከግብርና ስነ-ምህዳር ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ የመፍትሄ እርምጃዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

የቀረቡትን የጥናታዊ ፅሁፍ ፕሮፖዛሎች መሰረት በማድረግ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በአውደ ጥናቱ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት የጥናትና ምርምር ባለሙያዎችና የክብር እንግዶች ተገኝተዋል፡፡