የስርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ከሳይኮሎጂና ከማኔጅመንት ትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር ለሴት መምህራንና ለአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መጋቢት 9/2008 ዓ/ም የህይወት ክህሎት ስልጠና ሰጥቷል ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የስልጠናው ዓላማ ሴቶች በአመራርነት ሚና ያላቸው ተነሳሽነት እንዲጨምር ማድረግ እና እውቀታቸውን ተጠቅመው በመማር ማስተማር ሂደትም ሆነ በሌሎች የአመራር ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን የስርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ክንዱ ዘውዱ ገልጸዋል፡፡

የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ኢዮብ አየነው የህይወት ክህሎት ከሰዎች ጋር አብሮ ለመኖርና ለውጦችን ተላምዶ ለመስራት መቻል፣ አዎንታዊ አመለካከትን ማበልፀግና በህይወት ሂደት ውስጥ ፈታኝ ነገሮችን ተቋቁሞ ማለፍ እንዲሁም ከወቅታዊ ነገሮች ጋር አብሮ መሄድ መቻል ነው ብለዋል፡፡  በተጨማሪም ማህበራዊ ክህሎት በተፈጥሮ የሚገኝ ሳይሆን የሰው ልጅ በትምህርት፣ አብሮ በመኖርና በህይወት ቆይታ የሚያዳብረው ነው፡፡

ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ተቃራኒ ሃሳቦችን አስማምተው ራሳቸውንም ሆነ ሌላውን ሳይጎዱ ግባቸውን የሚመቱበት የማህበራዊ ክህሎት ስልጠና ወሳኝ እንደሆነ የሳይኮሎጂ የትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አንተነህ ዓለም ተናግረዋል፡፡ በራስ መተማመን፣ ራስን መረዳትና ለራስ ያለን ግምት ማሳደግ በግል ህይወትም ሆነ በስራ ዓለም ወደ ተሻለ ብቃትና ኃላፊነት ያመጣል፡፡ በመሆኑም ሥልጠናው ተሳታፊዎች ጠንካራ ጎናቸውን እንዲያጎለብቱና ክፍተቶችንም በሂደት እየገመገሙ እንዲሞሉ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

በአመራር ሂደት በአለም ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑን የገለፁት የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አብዮት ፀጋዬ ሴቶች አርቆ የማሰብ፣ የጠንቃቃነትና የሚያጋጥማቸውን ችግር ችሎ የማለፍ ብቃት ያላቸው ቢሆንም ወደ አመራርነት እንዳይገቡ የሚያደርጋቸው የአመለካከት ችግር እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአመራር ሂደት ውጤታማ ለመሆን መሟላት የሚገባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ ትክክለኛ ተግባቦት እንዳይካሄድ መሰናክል የሚሆኑና የተግባቦት ክሂልን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ጉዳዮችም በስልጠናው በስፋት ተዳሰዋል፡፡

ስልጠናው ለስራቸው የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የገለፁት ተሳታፊዎቹ ከዚህ ቀደም ወደ አመራርነት ለመምጣት ፍላጎቱ እንዳልነበራቸውና ስልጠናው በተደጋጋሚ በመሰጠቱ የአመለካከት ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡