የኘሬዝደንት ጽ/ቤት እና ም/ኘ/ጽ/ቤቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የ2008 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ሚያዝያ 5/2008 ዓ/ም አካሂደዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

በማብራሪያ፣ በሠንጠረዥና በፎቶ ተደግፎ የቀረበው ሪፖርት በ9 ወራት የተከናወኑ አበይትና ዝርዝር ተግባራትን እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አሳይቷል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደት በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑ፣ የተማሪ መጠነ ማቋረጥ መቀነሱ፣ የውሃ አቅርቦትን ለመጨመር የእቃ ግዥ መፈፀሙ፣ ለ91 የመጀመሪያ ደ/ት/ቤት መምህራን የሳይኮሎጂና ሥነ-ሰብ ት/ት ሥልጠና መሰጠቱ እንዲሁም 52 የሕክምናና በተለያዩ ት/ት ዘርፎች 920 ተማሪዎች መመረቃቸው አበይት ተግባራት ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

በአንፃሩ ማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በቂ ጥረት አለመደረጉ፣ በኤሌክትሪክና በኢንተርኔት መቆራረጥ እና በሌሎች ችግሮች SMISን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል፣ የመምህራን ፍልሰት፣ በማዕቀፍ ግዢ ምክንያት የግብዓት አቅርቦት መጓተት እና የውኃ አቅርቦት እጥረት ካጋጠሙ ችግሮች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የለውጥ መሳሪያዎችን በተለይም ካይዘን፣ ሚዛናዊ ውጤት ተኮር ሥርዓት እና የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት አደረጃጀትን በተጠናከረ ሁኔታ መተግበር፣ የታቀዱ የካፒታልና የመደበኛ በጀት አጠቃቀምን ማሻሻል እንዲሁም የግንባታ ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኘሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በቀሪ የዕቅድ ትግበራ ጊዜያት መልካም አፈፃፀሞችን በማጠናከርና ለተጠቀሱ ክፍተቶች አፅንኦት በመስጠት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በግምገማው የበላይ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የት/ት ክፍል ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በዕቅድ ክለሳና በዕቅድ ክንውን ምዘና እንዲሁም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው  ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡