የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬከቶሬት ተሽከርካሪዎችን መቆጣጠር የሚያስችል Arba Minch University Fleet Management and Tracking system (AMU-Fmts) ሶፍትዌር ትግበራ ግንቦት 25 2008 ዓ/ም የሙከራ መርሃ-ግብር አከናውኗል፡፡

በሙከራ መርሃ-ግብሩ ከዋናው ግቢ በኩልፎ ካምፓስ - ሲቀላ አደባባይ በGoogle መንገድ ቁጥር 7 ወደ ዋናው ካምፓስ የ20 ደቂቃ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ታዳሚዎች የተሽከርካሪውን እንቅስቃሴ በቀጥታ ተከታትለዋል፡፡ በዚህም የመኪናውን ፍጥነት፣ የአቅጣጫ ለውጥ፣ የቆመበትን ሠዓት፣ የሞተር መነሳትና መጥፋት (start/stop) እና ሌሎችንም መረጃዎች ማወቅ ተችሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ተሽከርካሪዎች በተወሰነ ሠዓት የት እንደሚገኙ ለማወቅ፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በየዕለቱ የሚመደቡ የሰርቪስ አገልግሎት አውቶብሶችን እንዲከታተል፣ በGoogle map የማይታወቁ ቦታዎችን በቀላሉ ለመረዳት እንዲሁም የወረቀትና ስልክ ተኮር ስራዎችን ለመቀነስ ያስችላል፡፡

በቀጣይ የተሽከርካሪን አላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሴንሰሮችን የመግጠም፣ የመኪናዎችን ውሎ አስመልክቶ ለስምሪት ክፍል አገልግሎት አስፈላጊ የSMS እና e-mail መልዕክቶች የሚላኩበትን ሥርዓት የመዘርጋት እና ሁሉንም የግቢውን ተሽከርካሪዎች በዚህ አገልግሎት ዉስጥ የማካተት ሥራ ይከናወናል፡፡ ሙሉ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ በአምስት የግቢው ተሽከርካሪዎች ላይ በቅርቡ ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን በ2009 ዓ/ም በሰፊው ለመተግበር ዕቅድ ተይዟል፡፡