የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ ቡድን ከአርባ ምንጭ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት፣ ከUNICEF እና UNFPA ጣምራ ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት ከአርባ ምንጭ ከተማና ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ 20 የጤና ባለሙያዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል ፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ኦፊሰር አቶ ኃይሉ ሽብሩ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተቀረፀው ፓኬጅ ላይ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ክፍሎችን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም መሰረታዊ የዕውቀት፣ የክህሎትና የአኗኗር ለውጥ በመፍጠርና የአገልግሎት ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ከኤች አይ ቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ማፍራት ነው፡፡ በተጨማሪም ህብረተሰቡ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ማስቆም የጋራ ሥራ መሆኑን ተገንዝቦ በባለቤትነት በመንቀሳቀስ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንዲችል የሚያደርግ ነው፡፡

የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል ሥራ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥሩ ሁኔታ ሲተገበር የቆየና ለውጥ የታየበት ቢሆንም ከሚፈለገው ደረጃ የደረሰ አይደለም ያሉት ኦፊሰሩ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ክህሎታቸውን በማሳደግና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት እንደ ሀገር የተቀመጠውን ራዕይ  ማሳካት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን እየተካሄዱ ካሉት ፈጣንና ሰፊ የልማት እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን መዝናኛዎችና የወሲብ ግብይቶች የሚስፋፉበት ዕድል ሰፊ መሆኑ፣ ተጋላጭነትን የሚያባብሱ የአኗኗርና የባህርይ ለውጦች መኖራቸው፣ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮሩ የፀረ-ኤች አይ ቪ ፕሮግራሞችና አገልግሎቶች አለመጠናከርና የተደራሽነት ውስንነቶች ለስርጭቱ መባባስ ስጋቶች መሆናቸውን በስልጠናው  የቀረቡት ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ ሀገራችን ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ /ኤድስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ሥርጭቱን ለመቀነስ በርካታ ጥረቶችን በማድረጓ ሀገር አቀፍ ሽፋኑን ወደ 1.2 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ውጤቱ በማህበረሰቡ ዘንድ መዘናጋትን በመፍጠሩ የቫይረሱ ሥርጭት በማገርሸት ላይ ነው፡፡ ስልጠናው መዘናጋት እንዳይኖርና ከበፊቱ በተሻለ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመግታት ብሎም በ2030 ለመድረስ የታሰበውን ከኤች አይ ቪ ነፃ ማህበረሰብ ለመፍጠር ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበሪያና መምሪያ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ወ/ጊዮርጊስ በዩኒቨርሲቲውና በከተማው በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች የኤች አይ ቪ መከላከል ስራ ላይ ትኩረት ሰጥተው ራሳቸውንና ሌሎችን ከበሽታው እንዲጠብቁ፣ ህብረተሰቡ በበጎ ፈቃደኝነትም ሆነ በባለሙያ ቅስቀሳ የምርመራ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆንና ቫይረሱ በደማቸው የተገኘ ግለሰቦች መድኃኒቱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም የኤች አይ ቪ ምርመራ ቢካሄድም ሁሉንም  ያማከለ  አለመሆኑን የገለፁ ሲሆን በቀጣይ ሰዎች ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ኖሯቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ጤና ተቋም በመምጣት ምርመራ እንዲያደርጉና ከቫይረሱ እራሳቸውንና ወገኖቻቸውን እንዲታደጉ የማድረግ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡