የኮምፒውተር ሣይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪዎች ክበብ ከግንቦት 22-23/2008 ዓ/ም 5ኛውን ዙር የ ICT ፌስቲቫልና አውደ ርዕይ በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ አካሂዷል፡፡

የአውደ ርዕዩ ዓላማ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር በማዋል ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን በተጨባጭ ለህብረተሰቡ ማሳየት የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ነው፡፡ በተጨማሪም ስለኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ የሚያሰፋ፣ ለሌሎች ተማሪዎች መነሳሳትና መነቃቃትን የሚፈጥር እና ትምህርት ክፍሉን በይበልጥ የሚያስተዋውቅ መሆኑን የኮምፒውተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ መሳይ ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ‘Online Taxi Reservation System for Addis Ababa Town’ ፣ ‘Online Complaint management’ ፣ ‘AMU Tube Hospital Management System’ እና ‘Online Bid’  ሶፍትዌሮች ቀርበዋል፡፡ የፈጠራ ሥራዎቹ ተግባራዊ ቢደረጉ የተለያዩ ተግባራትን የሚያቀላጥፉ ስለሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባና ከዚህ በተሻለ መልኩ ለመስራት የመምህራንና የሌሎች ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው የክበቡ ፕሬዝደንት ተማሪ ምንተስኖት ባዩ ተናግሯል፡፡ ስፖንሰር በማድረግ ለኤግዚቢሽኑ መሳካት ያገዛቸውን ሳታ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅንም  አመስግኗል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ተጠሪ መምህር ሲሳይ ቱምሳ በበኩላቸው ሀገሪቱ የምትፈልገውን በቴክኖሎጂ ብቁ የሆነ ዜጋ ከማፍራት አንፃር የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች በዓውደ ርዕዩ ለህብረተሰቡ ያቀረቧቸው የፈጠራ ሥራዎች ጥሩ ማሳያ ከመሆናቸው ባሻገር ተማሪዎቹ ለቴክኖሎጂው ቅርብ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ከቀረቡት ስራዎች መካከል ‘Online Taxi Reservation System for Addis Ababa Town’ በተመልካች ዕይታ በአንደኝነት በመመረጥ ሽልማት ያገኘ ሲሆን ከሰኔ 6-10 በሃዋሳ ከተማ በሚካሄደው ዓውደ ርዕይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆንም ተደርጓል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ሥራዎቻቸውን ላቀረቡ ከ1ኛ- 4ኛ ዓመት ተማሪዎች እንዲሁም ለፕሮግራሙ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተማሪዎችና የትምህርት ክፍሉ መምህራን የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡