የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ከጋሞ ጎፋ ዞን 15 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 35 ሰልጣኞች ከግንቦት 6/2008 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 13  ቀናት  የመረብ ኳስ ዳኝነት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በመረብ ኳስ ዳኝነት ረገድ በዞኑ ከፍተኛ የክህሎት ክፍተት በመኖሩ ይህንን ለመቅረፍና ብቁ የመረብ ኳስ ዳኞችን ለማፍራት ታስቦ ሥልጠናው መዘጋጀቱን የስፖርት አካዳሚ የክህሎት ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ በዛብህ አማረ ገልፀዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጠንክር ግዛቸው እንደተናገሩት  ዩኒቨርሲቲው ለዞኑ በሰጠው ኮታ መሰረት የስፖርት ዝንባሌ ያላቸው፣ ለብዙ ጊዜ ማገልገል የሚችሉና የተሟላ አካላዊ ብቃት ያላቸው ሠልጣኞች ተመልምለዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ቀደም ሲል በልምድ ሲዳኙ የነበሩ በመሆናቸው  ህጉን ጠንቅቀው በማወቅ የዳኝነት ችግሮችን እንዲቀርፉ ስልጠናው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

ከሀዋሳ የመጡት አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ትዕግስቱ ቀቀቦ አካዳሚው ወደ ማህበረሰቡ በመዝለቅ በስፖርቱ ዙሪያ ያለውን የክህሎት ክፍተት ለይቶ ስልጠና ማዘጋጀቱ ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን ተናግረው ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተሞክሮውን ሊቀስሙ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሠልጣኞች ባገኙት ክህሎት ቀደም ሲል የሚስተዋሉ ችገሮችን በመቅረፍ የአሰራር ለውጦችን እንደሚያመጡ ብሎም ሥልጠናውን ላላገኙ ሌሎች ባለሙዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል አቅም ማጎልበታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከስልጠናው በኋላ በተሰጠው የማጠቃለያ ፈተና መሰረት አመርቂ ውጤት ላመጡ ሰልጣኞች የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን 2ኛ ደረጃ ስልጠና እንዲያገኙ የሚመቻች መሆኑም ተገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከእግር ኳስና ከቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመቀናጀት ለ68 አማተር ባለሙያዎች የእግር ኳስና የቅርጫት ኳስ ስልጠና የሰጠ ሲሆን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያም ምልመላዎችን በማካሄድና በስልጠናው ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ እየተወያዩ በመፍታት የማስተባበር ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡