በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የሚቲዮሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ትምህርት ክፍል ሆላንድ ከሚገኘው ዋግኒንገን /Wageningen UR/ ዩኒቨርሲቲ የሚቲዮሮሎጂና የአየር ጥራት ትምህርት ክፍል ጋር በመቀናጀት በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች የአየር ንብረት፣ የአፈር እርጥበትና የፀሃይ ጨረር መጠንን የሚለኩ ስድስት አውቶማቲክ መሳሪያዎች ተከላ አካሂዷል፡፡ የመሣሪያ ተከላውን አስመልክቶም ሚያዝያ 1/2008 ዓ/ም የልምድ ልውውጥና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዓውደ ጥናት በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ተዘጋጅቷል፡፡

መሳሪያዎቹ በዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ የPHD ምሁር ቶማስ ቶሮራ ‹‹Weather Research and Forecasting model›› በመጠቀም በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች የአየር ጠባይ ለውጥ በሰብል ምርት በተለይም በድቡልቡል ድንች ላይ ያለውን ተፅዕኖ በሚመለከት እያካሄደ ላለው የምርምር ስራ እንዲረዱ የተገዙ ሲሆን በአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ፣ ኦቾሎ፣ ጨንቻ፣ ዚጊቲ ባቆሌ እና በቦንኬ ወረዳ ጌዜሶ አካባቢዎች ተተክለዋል፡፡

አውደ ጥናቱ በሞዴሉ ላይ ግንዛቤን ለማስጨበጥ፣ የትምህርት ክፍሉ መምህራን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ በዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ የPHD ትምህርታቸውን ተከታትለው በዘርፉ በቂ የሰው ኃይል ማፍራት ለማስቻል እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለውን የአቻ ለአቻ ግንኙነት ማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የትምህርት ክፍሉ መምህር አቶ ሙሉጌታ ገናኑ ተናግረዋል፡፡

የPHD ምሁር ቶማስ ቶሮራ ባካሄዱት ከፊል የምርምር ስራ እ.ኤ.አ ከ2001 - 2010 ያለውን የ10 ዓመት የድንች ምርት፣ የበልግ ወቅት ጅማሮ፣ አስተማማኝ ዝናብና ምቹ የአየር ሁኔታ የሚኖርበት ጊዜ እንዲሁም ውጤታማ የዘር ወቅትን በሞዴሉ ተመርኩዞ መተንበይ ተችሏል፡፡ የተጀመረው ምርምር ሲጠናቀቅ መሳሪያዎቹ በተተከሉበት ቦታ አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ በአውደ ጥናቱ ተገልጿል፡፡

Dr. ir. Michiel van der Molen ከዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ ከሚቲዮሮሎጂና የአየር ጥራት ትምህርት ክፍል መሳሪያዎቹ በአግባቡና በሚፈለገው ቦታ መተከላቸውን ለማረጋገጥና ተከላውን ለማገዝ የመጡ ሲሆን በአውደ ጥናቱ ላይ የዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲን አጠቃላይ ገፅታ አስቃኝተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከአርሶ አደሮችም ጋር በጋራ መስራት የሚቻልበትን አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ሌሎች በትምህርት ክፍሉ የተሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችም ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመ/ር ሙሉጌታ ገናኑ የወንጂ ሸንኮራ አገዳ ምርት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍና በመ/ር አሰፋ ደርበው የህንድ ውቅያኖስ የሙቀት መጠን በምስራቅ አፍሪካ የዝናብ ሁኔታ ላይ ያለውን ተፅዕኖ የሚያሳየው ጽሑፍ ይጠቀሳሉ፡፡ ጥናታዊ ጽሁፎቹን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከታዳሚዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡