ዓለም አቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ቀን ‹‹Hotter, Drier, Wetter. Face the future.›› በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 14 /2008 ዓ/ም በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ የበዓሉ ዓላማ በሰው ልጆች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚፈጠረውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ማሳደግ፣ ከሳይንሱ ጋር የተያያዙ መረጃዎችና እውነታዎችን ማስጨበጥ እንዲሁም ችግኞችን መትከልና አካባቢን መንከባከብ እንዳለብን ማስታወስ መሆኑን የሚቲዮሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ሙሉጌታ ገናኑ ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ያስቀመጠውን ደረጃ ጠብቆና አስፈላጊ መሳሪያዎችን አሟልቶ በአባያ ካምፓስ የተገነባው የሚቲዮሮሎጂ ምልከታ ጣቢያ ምረቃ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡ የ250 ችግኞች ተከላ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ጭፈራ እንዲሁም የጥያቄና መልስ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን በውድድሩ ለተሳተፉና ከየባቹ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የትምህርት ክፍሉ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በሀገራችን አብዛኛውን ጊዜ ድርቅን እያስከተለ ያለው የአየር ንብረት መዛባት እንደሆነ የገለፁት የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤል የሚቲዮሮሎጂ የምልከታ ጣቢያ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በዩኒቨርሲቲው መቋቋሙ የአካባቢውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ለህብረተሰቡ የአየር ንብረት መረጃ በማድረስ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የተለያዩ የአየር ንብረት ክስተቶች ከመፈጠራቸው በፊት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያግዛል፡፡ የምልከታ ጣቢያው ለመማር ማስተማርና ለምርምር ስራ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡
ዓለም ዓቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ በኦስትሪያ ቬና እ.ኤ.አ በ1873 ተቋቁሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና ያገኘ ሲሆን ዓለም ዓቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ቀንም ድርጅቱ የተመሰረተበትን ቀን በማሰብ እ.ኤ.አ ከ1950 ጀምሮ በተለያዩ መሪ ቃሎች እየተከበረ ይገኛል፡፡