ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ጎፋ ዞን ለቦንኬ ወረዳ 1ኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል ት/ቤቶች መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከመጋቢት 10/2008 ዓ/ም ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

በትምህርት ቤቶቹ ባለው የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት የማስተማር ስነ-ዘዴ ስልጠና ሳይወስዱ በማስተማር ሥራ ላይ የተሰማሩ መምህራንን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት የትምህርት ጽ/ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ስልጠናው መዘጋጀቱን የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ አሰግደው ሽመልስ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው በማህበራዊ ሳይንስና ሰነ-ሰብ ኮሌጅ መምህራን የተሰጠ ሲሆን በዋናነት የትምህርት ስነ-ባህርይ፣ የማስተማር ስነ-ዘዴ፣ የተከታታይ ምዘናና ግምገማ እንዲሁም የጋሞኛ ቋንቋ አጠቃቀም በክፍል ውስጥ በሚሉ ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በስልጠናው ማጠቃለያ እንደተናገሩት የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ተግባር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ሊሠራበት የሚገባ በመሆኑ ታዳጊ ተማሪዎችን ከመሰረቱ በእውቀትና በሥነ-ምግባር ማነጽ ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመምህራንን አቅም ማጎልበት ተገቢ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራን የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በማስተማር ስነ-ዘዴም ሆነ በትምህርት ስነ-ባህርይ ላይ ምንም ግንዛቤ ሳይኖራቸው በልምድ ብቻ ሲያስተምሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በስልጠናው ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ወደ ተግባር በመቀየር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

በስልጠናው ከ90 በላይ ሰልጣኝ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን በማጠቃለያው ለአሰልጣኞችና ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በዕለቱ እንግዶች ተበርክቷል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የማህበረሰቡን የትምህርት፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስና ቴክኖልጂ፣ የጤና፣ የአካባቢና ማህበራዊ ልማት ፍላጎቶችን የሚያጎለብቱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽዎ እያበረከተ ይገኛል፡፡