የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት የ2008 ዓ/ም የበጀትና ዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ ሰኔ 12/2008 ዓ/ም ግምገማ አካሂዷል፡፡ የተማሪዎች ህብረት ተተኪ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫም ተከናውኗል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የግምገማው ዓላማ ህብረቱ ያከናወናቸውን በጎ ተግባራትና ክፍተቶች በመለየት ለተሻለ ሥራ ማነሳሳት መሆኑን የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝደንትና የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪ ዮርዳኖስ መኩሪያው በህብረቱ የተከናወኑ ተግባራትን ሪፖርት ሲያቀርብ ገልጿል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በዩኒቨርሲቲው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ለተጫወተው  ሚና የተማሪዎች ህብረት እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም ህብረቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት የበለጠ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ ህብረቱ ከሠላም ፎረም ጋር ተቀናጅቶ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው የምክር አገልግሎት ተግባራት፣ የልማት ሠራዊት ግንባታ ሪፖርቶችን ወቅታዊ ማድረግ፣ የሴት ተማሪዎች ክበብን ወደ ፎረም ደረጃ ማሸጋገር እና የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ተማሪዎችን ለይቶ መፍትሔ መስጠት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ዮርዳኖስ መኩሪያው የዩኒቨርሲቲ ቆይታውን አጠናቆ በዘንድሮው ዓመት የሚመረቅ በመሆኑ በዕለቱ ተተኪ ፕሬዝደንትና ሥራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል የተማሪዎች ዲሲፕሊን ተጠሪ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ተማሪ ጌታቸው ወርቁ የህብረቱ ፕሬዝደንት ሲሆን ሌሎች ሥራ አስፈፃሚ አባላትም ተመርጠዋል፡፡ ተተኪ ሥራ አስፈፃሚ አባላቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋት እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል፡፡