የሳውላ ካምፓስ የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የውል ስምምነት ተፈረመ

ዩኒቨርሲቲው ከዩናይትድና ከብራይት ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር የ2ኛ ዙር የሳውላ ካምፓስ የግንባታ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ውል ሰኔ 28/2008 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ዩናይትድ ኮንስትራክሽን ከአስር ተጫራቾች መካከል ዝቅተኛ ዋጋ ብር 37,738,693.88 (ሰላሳ ሰባት ሚሊየን ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሶስት ብር ከሰማኒያ ስምንት ሳንቲም) በማስገባት የሎት አንድ አሸናፊ በመሆኑ መማሪያ ክፍሎች ፣ላቦራቶሪ እና ላውንደሪ ህንጻ ግንባታ በአንድ አመት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ውል ፈርሟል፡፡

ብራይት ኮንስትራክሽን ከሰባት ተጫራቾች መካከል ዝቅተኛ ዋጋ ብር 96,870,962.69 (ዘጠና ስድስት ሚሊየን ስምንት መቶ ሰባ ሺ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሁለት ብር ከስልሳ ዘጠኝ ሳንቲም) በማስገባት የሎት ሁለት አሸናፊ በመሆናቸው ካፍቴሪያ፣ ላይብረሪ፣ አጥር እና የምድረግቢ ሥራ (ሳይት ወርክ) በአንድ አመት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ውል ፈርሟል፡፡  

የማስፋፊያ ግንባታው ለመማር ማስተማርና ለምርምር ስራዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር የትምህርት ጥራትን ለማሳካት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን እቅድ ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ አሸናፊ ተቋራጮችም ይህንን በመገንዘብ የገቡትን ውል በተቀመጠው የጊዜ ገደብና ጥራት በታማኝነት መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዝደንቱ የውል ስምምነቱን በሚፈርሙበት ወቅት አሳስበዋል፡፡

አሸናፊ ተቋራጮች ግንባታውን ለመጀመር በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ማሽነሪዎች ማዘጋጀታቸውንና ግንባታውን በገቡት ውል መሠረት ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን እንዲሁም ችግሮች ሲከሰቱ ከዩኒቨርሲቲው፣ ከሚመለከታቸው አካላትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት ለመፍታት ቃል ገብተዋል፡፡