ዩኒቨርሲቲው ከደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ/ አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመተባበር በአነስተኛ መስኖ አስተዳደርና አጠቃቀም ለ6 ወራት ያሠለጠናቸውን 30 ሠልጣኞች ግንቦት 13/2008ዓ.ም አስመርቋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት/ም/ፕ/ ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እንደገለጹት ተመራቂዎቹ ባገኙት እውቀትና ክህሎት የከርሰ ምድር ውኃን ተጠቅመው ለተለያዩ የአፈር ዓይነቶች በተስማሚ ስልት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን እና ማህበረሰባቸውን እንዲጠቅሙ ሥልጠናው ከፍተኛ እውቀት ያስጨብጣል::

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ/ አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ ጊንዶ እንደተናገሩት በደቡብ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከተያዙ የልማት ፕሮግራሞች አንዱ የመስኖ ፕሮግራም ሲሆን በተለይም ድርቅ በሚያጠቃቸው ቦታዎች ወንዞችን በመጥለፍ በአመት 3ጊዜ ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ፕሮግራሙ አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርሶ አደርነት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው፡፡ አርብቶ አደሩ በጥራትና በብዛት አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆንም ያስችላል፡፡

ሠልጣኞቹ ከ3 ዞኖችና ከ12 ወረዳዎች የተመለመሉ ሲሆን በከርሰ ምድር ውኃ አጠቃቀምና መስኖ ጠለፋ፣ አፈርና ማሣ ዝግጅት፣ ተባይ መከላከል፣ የጓሮ አትክልት ልማት እና ድህረ ምርት አያያዝ በንድፈ ሀሣብና በተግባር የታገዘ ሥልጠና አግኝተዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በአስተያየታቸው ‹‹በሥልጠናው ባካበትነው እውቀትና ክህሎት አርብቶ አደር ወገናችንን በሳይንሳዊ የመስኖ አሠራር ተጠቃሚ ለማድረግ ቃል እንገባለን›› ብለዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ/አርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና ባለሙያዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና የተመራቂ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎች የምስክር ወረቀትና አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ ሰልጣኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡