ለትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ግንባታ ተገቢው ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተገለጸ

የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት በለውጥ ስራዎች አተገባበር ደረጃ እና በመማር ማስተማር አፈፃፀም ላይ ግንቦት 16/2008 ዓ/ም ውይይት አካሂደዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የውይይቱ ዓላማ እየተገባደደ ባለው የ2008 የትምህርት ዘመን በመማር ማስተማር ሂደት እንዲሁም በትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት አተገባበር ላይ የታዩ ክፍተቶችን በጋራ መለየትና በቀሪ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ወደ ስራ መግባት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ እንደተገለጸው የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ትግበራ በአመራር፣ በአስተዳደር ሠራተኛውና በተማሪው በኩል የተሻለ አፈፃፀም ያለው ሲሆን በአንፃሩ የመምህራን አፈፃፀም ክፍተቶች ተስተውሎበታል፡፡ በመሆኑም ትምህርት ክፍሎች ውጤት ተኮር አሠራርን መሰረት በማድረግ እንዲተገብሩና በተለይም ለተማሪዎቻቸው መልካም አርአያ እንዲሆኑ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕ/ ልዩ ረዳት አቶ አብዮት ፀጋዬ ባቀረቡት ሪፖርት በ2ኛው ወሰነ ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄዱ፣ ሞጂላራይዜሽን በሁሉም ት/ት ክፍሎችና ኮሌጆች ተግባራዊ መደረጉ፣ መፅሐፍትን ለማሟላት ጥረት መደረጉ እና የመምህራን ተሳትፎና እንቅስቃሴ መሻሻሉ ጠንካራ ጎኖች ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አለመከናወኑ፣ በመምህራን ዘንድ ተማሪ ተኮር የትምህርት አሰጣጥና የተከታታይ ምዘና አተገባበር አጥጋቢ አለመሆኑ እንዲሁም በትምህርትና ቴክኖሎጂ ሠራዊት ልማት የክፍል ተጠሪ መምህራን ላይ ክፍተት መኖሩ ተመልክቷል፡፡

የትምህርትና ቴክኖሎጂ ሠራዊት ልማት ግንባታን መከለስ፣ ማጣቀሻ መጽሐፍትን ማሟላት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው እና ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎችን በመጋበዝ በተማሪ ተኮር ትምህርት አሠጣጥና በምዘና ሥርዓት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ማዘጋጀት በቀጣይ የአፈፃፀም ጊዜያት ለመተግበር በዕቅድ መያዛቸው በውይይቱ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡