ከመስከረም 05-12/2008 ዓ/ም ለአንድ ሣምንት የሚቆየው የከፍተኛ ትምህርት ማህበረሰብ ሥልጠና በዩኒቨርሲቲው ሦስት የተለያዩ አዳራሾች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ስልጠናው አምስት የተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት የሚመክር ሲሆን ለውይይት አመቺ እንዲሆን ሠልጣኞች በበርካታ ቡድኖች ተከፋፍለዋል፡፡ የሥልጠናዉን ተሳታፊዎች በከፍል ለማየት እዚህ ይጫኑ

በስልጠናው የመጀመሪያ ቀን ውሎ በሀገሪቱ የሩብ ምዕተ ዓመት የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ፣ የከፍተኛ ትምህርት ሚናና ቀጣይ ተልዕኮ ላይ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በዚህም ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተመዘገቡ አንኳር ሀገራዊ ለውጦች፣ በትምህርት መስክ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች፣ ለኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ መገንባትና ለሀገራችን ህዳሴ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሊኖረው የሚገባው ቁመናና ቀሪ ሥራዎች እንዲሁም በቀጣይ ጊዜያት የባለድርሻዎች ሚና ላይ ተሳታፊዎች ውይይት አካሂደዋል፡፡

በተጨማሪም በፖለቲካው መስክ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ላይ መሆኑንና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮችም እንዲሁ ስኬቶች መመዝገባቸው ተወስቷል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ ለሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መፍትሄ ከማምጣት ባለፈ በሀገሪቱ ሰላማዊ ሂደት እንዲሰፍን የጎላ ሚና መጫወቱ የተገለጸ ሲሆን ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት የአመለካከት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ሌሎች በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ከውስጥም ከውጭም እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡

በስልጠናው ከ1050 በላይ መምህራንና ከ1883 በላይ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በሰነዱ መነሻነት  የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው በዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የቦርድ አባላትና በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ምላሽና አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናው ቀጣይ ቀናት ‹‹በሀገራችን አንድ የጋራ ማህበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነት›› እና ‹‹የትምህርት ጥራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት›› በሚሉ አጀንዳዎችና በዩኒቨርሲቲው የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት