የ2008 ዓ/ም የዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባላት ከነሐሴ 6-7 የመስክ ምልከታ አካሂደዋል፡፡

የቦርድ አባላቱ በአርባ ምንጭ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ባለ 6 ፎቅ ሪፈራልና የማስተማሪያ ሆስፒታል፣ በዩኒቨርሲቲው ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት ግንባታቸው የተጠናቀቀ የ2ኛ ደረጃና የመሰናዶ ተማሪዎች የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-ሙከራዎችና ቤተ-መጽሐፍት፣ በተለያዩ ኮሌጆች በግንባታ ላይ የሚገኙ ቤተ-መጽሐፍት፣ ቤተ-ሙከራዎች፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ አዳራሾች፣ የአርክቴክቸር ድሮዊንግ ስቱዲዮዎች፣ የመምህራንና የአስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገዶችን ተዘዋውረው በመጎብኘት የግንባታ ሂደቱን ገምግመዋል፡፡

የማስፋፊያ ስራዎቹ በርካታ በመሆናቸው ጥራታቸው እንዳይጓደልና በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ጠንካራ ክትትል ያስፈልጋል ያሉት የቦርዱ አባል ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማርያም ግንባታዎቹ የዩኒቨርሲቲውን ብሎም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ በመሆናቸው አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ግብዓቶች ተሟልተው ለአገልግሎት ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከመስክ ምልከታው በኋላ በተዘጋጀው የጋራ መድረክ የ2008 ዓ/ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የቀረበ ሲሆን ከተከናወኑ የላቁ ተግባራት መካከል ከቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር መፈጠሩ፣ በጋሞኛ እና ጎፍኛ ቋንቋዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም መጀመሩ፣ በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር የመማር ዕድል ያላገኙ 167 ጎልማሶችን አስተምሮ በደረጃ ሁለት ማስመረቁና ውጤታማ የ1ለ5 የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊት መገንባት መቻሉ ተጠቃሽ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ዶ/ር ዳምጠው አክለውም በቀጣይ የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት አደረጃጀትን በመጠቀም ዝቅተኛ አፈፃፀም ለተመዘገበባቸው ተግባራት ትኩረት መስጠት፣ የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረም ውይይቶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና ከአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጋር የተያያዙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የለውጥ መሳሪያዎች በተለይም ካይዘንና ሚዛናዊ ውጤት ተኮር ስርዓት በተጠናከረ ሁኔታ መተግበራቸውን ማረጋገጥና ከግዢ ጋር በተያያዘ ያለውን የግብዓት አቅርቦት ስርዓት ማሻሻል ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታገሰ ጨፎ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው መውጣታቸው ለቀጣይ ትግበራ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የማስፋፊያ ግንባታዎች ሥራ፣ ቋሚ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ መቋቋሙና የመማር ማስተማሩ ሂደት  ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ብሎም ለሂደቱ ስኬታማነት የሠላም ፎረም እንቅስቃሴ የተጠናከረ መሆኑ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፤ በአንፃሩ በአንዳንድ አፈፃፀሞች ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች መስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡