ዩኒቨርሲቲው በኮንሶ ካልድሜ ንዑስ ቀበሌ ያሠራውን የውሃ ማሸጋገሪያ ድልድይ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረከበ

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በኮንሶ ካልድሜ ንዑስ ቀበሌ ያሠራውን የውሃ ማሸጋገሪያ ድልድይ ሐምሌ 23/2008 ዓ.ም ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረክቧል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የካልድሜ፣ ሃዋይድ እና ቢሰቴ ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም  በባህላዊ  መንገድ ከያንዳ ወንዝ ውሃ ጠልፎ ይጠቀም ነበር፡፡ ነገር ግን ባህላዊ የውሃ መስመሩ በአፈርና በደለል በመሞላቱና በቂ ውሃ ማግኘት አዳጋች በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የውኃ ማሸጋገሪያውን ገንብቷል፡፡ ይህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በእጅጉ እንደሚያሳድገው የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ያንዳ ወንዝ ላይ የጎርፍ መቀልበሻ በማስገንባቱ በ0.3 ሄክታር መሬት ላይ ያገኙ የነበረውን 3 ኩንታል ምርት ወደ 15 ኩንታል ያሳደገው መሆኑን አውስተው የውሃ ማሸጋገሪያ ድልድይ ግንባታው ምርቱን አሁን ካለበት የተሻለ እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡ በውኃ ችግር ምክንያት የእርሻ መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ዳግም ለእርሻ ሥራ በማዘጋጀት ላይ ሲሆኑ መሠል የልማት ሥራዎችን በቅንጅት ለማከናወን የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሀይድሮሊክስና ውሃ ሀብት ት/ት ክፍል መምህር አቶ መልካሙ ተሾመ ግንባታው 280 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችልና 900 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ህብረተሰቡ የተረከበውን ግንባታ በባለቤትነት በአግባቡ እንዲገለገልበትም አሳስበዋል፡፡