ዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል

የግርጫ ደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል የመስክ ጉብኝት ጥቅምት 12/2009 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲው እየተሠሩ የሚገኙ ምርምሮች በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲተዋወቁ ማድረግና እየተጠናቀቀ የሚገኘውን የምርምር ማዕከል ግንባታ ምልከታ ማድረግ ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በእንሰት፣ በአፕል እና በተሻሻሉ የካሮት፣ ነጭ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን ዝርያዎች ላይ ገለፃ  አድርገዋል፡፡ የተሻሻሉት የካሮት፣ ነጭ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን ዝርያዎች ከደብረዘይት ምርምር ማዕከልና ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የተገኙ ሲሆን የተለያዩ የእንሰት ዝርያዎች ከአረካ የግብርና ምርምር ማዕከል በማስመጣት ከአካባቢው ሥነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑትን የመለየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በሀገራችን አፕል ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው በጨንቻ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ከቤተክርስቲያኑ የአንድ ዓመት ዕድገት ያላቸው ዘጠኝ የአፕል መሠረተ ግንዶች ወደ ምርምር ማዕከሉ ተወስደው እያንዳንዱ መሠረተ ግንድ በራንደማይዝድ ብሎክ ተተክሎ 50 የተለያዩ ዝርያዎች ነሀሴ 2008 ዓ.ም ተዳቅለዋል፡፡

በማዕከሉ 50 የተለያየ ዝርያ ያላቸው 1724 የአፕል ችግች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገ ነው፡፡ በዘመናዊ አፕል ዕድገት አስተዳደር አያያዝ በመተግበር የተሻሉና የተመረጡ ዝርያዎችን ለማግኘት እየተሠራ ነው፡፡ ዝርያዎቹ ከመሠረተ ግንዱ ጋር በሚፈጥሩት የተጣጣመ ውህደት ምርጥ ዝርያዎችን በማግኘትና ለይቶ በማባዛት ለማህበረሰቡ ለማዳረስ እየተሠራ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲዎች በኢኮኖሚው የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት በተጨማሪ በሚገኙበት አካባቢ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን ብሎም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው መንግሥት በፖሊሲው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይህ የግርጫ ደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል ሥራ ዩኒቨርሲቲው በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በግብርናው ዘርፍ የምርምር ሥራውን በማጠናከር ወደፊት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከያዛቸው ዕቅዶች ዋነኛው ሲሆን ማዕከሉ ዓላማውን በተሟላ ሁኔታ ሲያሳካ የአካባቢው ህብረተሰብ የማዕከሉ ውጤት የመጀመሪያ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

ወረዳው በኤዞ ቱላና ኦቴ አካባቢ በሰጠው 33 ሄክታር መሬት ላይ እጅግ ዘመናዊ የተመራማሪዎች ህንፃ እየተገነባ ሲሆን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ያሉ በማህበራት የተደራጁ ሴቶችና ወጣቶችን በዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎች በማሳተፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሚሆን የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ ገልፀዋል፡፡ በምርምር የተገኙ የተሻሉ ዝርያዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የአፈፃፀም ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ጅምር ሥራ ሊበረታታ የሚገባውና የማህበረሰቡን ምርታማነት የሚያሻሽል መሆኑን የጨንቻ ወረዳ ግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ገልፀዋል፡

የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ከበደ ጆቢር የአካባቢው ማህበረሰብ የምርምር ማዕከሉን እንደራሱ ሀብት ሊንከባከበው፣ ሊጠብቀውና በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በመስክ ጉብኝቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ባለድርሻ አካላት፣ የሚመለከታቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች እና የወረዳ ሴክተር መስሪያ ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡