አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2009 የትምህርት ዘመን አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን ሊያስጀምር ነው

ዩኒቨርሲቲው በያዝነው የትምህርት ዘመን 9 የፒኤችዲ፣ 32 የማስተርስና 15 የቅድመ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለማስጀመር ቅድመ ሁኔታዎችን ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች 10 በመቶው የድህረ ምረቃ ፕሮግራም እንዲከታተሉ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ የአዳዲስ ፕሮግራሞቹ መከፈትም በየዘርፉ ብቁና ተፎካካሪ የሰዉ ኃይል ለማፍራት የሚያስችል ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አቻ ተቋማት ጋር በትምህርትና በምርምር ያለውን ትሥሥርም ያጠናክራል፡፡

የፕሮግራሞቹ መከፈት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለገበያዉ ተመራጭና ተፎካካሪ፣ በመማር ማስተማሩና በምርምር ስራ ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ እና በየዘርፉ ብቁ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ልዩ ረዳት አቶ አብዮት ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡ ይህም ዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በአካዳሚኩ ዘርፍ ከሚያከናዉናቸዉ ተግባራት ተጠቃሽና የተቀመጠዉን ስትራቴጂክ ግብ ለማሳካት ፋይዳ ያለው ነው፡፡

የትምህርት ፕሮግራሞቹ ሲቀረፁ የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ቅድሚያ በሰጣቸው ዘርፎች ላይ ትኩረት መደረጉንና ለተማሪዎች ምቹ የልምምድና የሥራ ዕድል ያላቸው መሆኑ በዳሰሳ ጥናት መፈተሹን አቶ አብዮት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የሚታወቅበትን የውኃ ምህንድስና ዘርፍ ይበልጥ በማጠናከር በአፍሪካ ደረጃ እውቅና የሚያሰጡ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱና ሰፊ የሥራ ዕድል ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ሁሉም ፕሮግራሞች ውስጣዊና ውጫዊ የሥርዓተ የትምህርት ግምገማ የተከናወነባቸው ሲሆን ለፕሮግራሞቹ ስኬትም ዩኒቨርሲቲው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር መምህራን ቅጥር ፈጽሟል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራትና ከኩባ ተጨማሪ የሰው ኃይል ለማስመጣትም ዕቅድ ይዟል፡፡