የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶ አርካቶ በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል

ዶ/ር አንቶ አርካቶ ከአባታቸው አቶ አርካቶ ገንዶሌ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ካሚቴ ካይሪዮ በኮንሶ ወረዳ ዴበና ቀበሌ ጥር 20/1965 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፋሻ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮንሶ መ/2ኛ ደረጃና በጊዶሌ ከ/2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ በ1989 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አግኝተዋል፡፡

ከሐምሌ 01/1989 - ጥር 30/1991 ዓ.ም በዳሞት ወይዴ ወረዳ በበዴሳ መ/2ኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት፣ ከየካቲት 01/1991 - የካቲት 12/1992 ዓ.ም በኮንሶ ባህል፣ ማስታወቂያና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊነት እና በኮንሶ መ/2ኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት አገልግለዋል፡፡

የካቲት 13/1992 ዓ.ም በረዳት ምሩቅ ıı ማዕረግ የቀድሞውን አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተቀላቀሉ ሲሆን ከሚያዝያ 6/1994 ጀምሮ በረዳት ሌክቸረርነት እንዲሁም ከሐምሌ 17/1996 ዓ.ም የማስተርስ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ special Education በማጠናቀቃቸው በሌክቸረርነት አገልግለዋል፡፡

ከመስከረም 19/1997 ጀምሮ የማኅበራዊ ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው ነሀሴ 1997 ዓ.ም ለትምህርት ወደ ኔዘርላንድስ ሀገር ሄደዋል፡፡ በዚያም በካሪኩለምና ኢንስትራክሽን ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከቱዌንቴ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

ከየካቲት 1999 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ADRC አስተባባሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው ነሀሴ 2001 የፒኤችዲ ትምህርታቸውን ለመከታተል በድጋሚ ወደ ኔዘርላንድስ ሀገር ሄደዋል፡፡ ከኔዘርላንዱ ቱዌንቴ ዩኒቨርሲቲ በTeacher Professional Development የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ ከታህሣሥ 02/2006 ዓ.ም ጀምሮም የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተው ከሚያዝያ 07/2006 ዓ.ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ ጥቅምት 27/2009 ዓ.ም በተወለዱ በ44 ዓመታቸው በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ዶ/ር አንቶ በሥራቸው እጅግ ትጉህና ታታሪ ሲሆኑ በተሰጣቸው ኃላፊነት መንግሥትንና ህዝብን በታማኝነት፣ በቅንነትና በትህትና ያለመሰልቸት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሥራ አጋሮቻቸው፣ የአካባቢው ነዋሪና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ጥቅምት 29/2009 ዓ.ም በኮንሶ ወረዳ ዴበና ቀበሌ ተፈፅሟል፡፡

ዶ/ር አንቶ ባለትዳር እና የ2 ወንዶችና የ3 ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዶ/ር አንቶ አርካቶ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦች፣ ለወዳጅ ዘመዶችና ለሥራ ባልደረቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት