ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ብቁ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የተማሪዎች አደረጃጀቶች እንዲቋቋሙ በማገዝ ለውጤታማነቱም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በማቀራረብ በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

 

ፎረሙ ህዳር 15/2006 ዓ/ም የተቋቋመ ሲሆን ዓላማውም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህልን በማዳበር ተማሪዎች እርስ በእርስ፣ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት ማጎልበት እንዲሁም በሀገር ፍቅርና በሕብረ ብሄራዊነት የሚያምን እና ለሀገር ሀብትና ንብረት ተቆርቋሪ ትውልድ እንዲፈጠር ማስቻል ነው፡፡

ፎረሙ ተማሪዎች የተለያዩ የውጭ አካላት አፍራሽ ተልዕኮ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር፣ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በግልጽ በመወያየትና በመከባበር የመፍታትና በዩኒቨርሲቲው የሰላም ባህል የሚያጎለብቱ አዎንታዊ አመለካከቶች የማዳበር ሥራዎችን አጠናክሮ እየሠራ እንደሚገኝ የፎረሙ ፕሬዝደንት ተማሪ ሞላልኝ ኤልያስ ገልጿል፡፡ ፎረሙ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የነባርና አዲስ ተማሪዎች ቅበላ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈፀም የበኩሉን ድርሻ የተወጣ ሲሆን ቀጣይነቱን ለማረጋገጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ፎረሙ በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች አደረጃጀቶች ያሉት ሲሆን ከየትምህርት ክፍሎች ሁለት ተወካዮች በአጠቃላይ ሰማንያ አስፈፃሚ አባላትን ይዟል፡፡ ፎረሙ በሳውላ ካምፓስ ተደራጅቶ መሰል ተግባራትን እንዲያከናውን የሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ በቅርቡ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

 

(Corporate Communication Directorate)