ዩኒቨርሲቲው በ2009 የትምህርት ዘመን የተማሪ ቅበላ፣ የትምህርት ክፍል መረጣና ሌሎች የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን በማከናወን የመማር ማስተማር ሂደቱን በስኬት መጀመሩን ገልጿል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ እንደተናገሩት በዝግጅት ምዕራፍ መሠረታዊ የተማሪ ፍላጎቶችን ማሟላት እንዲሁም የተማሪዎች አቀባበልን በአግባቡ ማከናወን መቻሉ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በዝግጅት ምዕራፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት፣ የተማሪዎች ዶርም ድልደላ፣ የምግብ ጥሬ ዕቃዎችና መድኃኒቶች ግዢ፣ የጸረ-ተባይ መድኃኒት ሥርጭት፣ የስነ-ምግባር መመሪያና የተማሪዎች ሚል ካርድ ዝግጅት  ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በሁሉም ኮሌጆች ትምህርት በታቀደለት ጊዜ እንዲጀመር በመደረጉ በትምህርት ዘመኑ ‹የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ› አተገባበር ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ 90 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ገልፀዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ 6,125 መደበኛ አዲስ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉ ሲሆን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 1,948፣ ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ 427፣ ህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ 415፣ የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ 1,233፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ 1,122፣ ማህበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ 912 እንዲሁም ህግ ትምህርት ቤት 68 ተማሪዎች ተመድበዋል፡፡

የትምህርት ክፍል ምደባው ነጥብን፣ ፍላጎትን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትንና ኋላቀር አካባቢዎችን መሠረት አድርጎ በመከናወኑ ምደባውን አስመልክቶ የጎላ ቅሬታ አለመቅረቡን የሬጅስትራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ ተናግረዋል፡፡

አዲስ ገቢ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ በሠላም ፎረም፣ በተማሪዎች ህብረት፣ በነባር ተማሪዎች፣ በዩኒቨርሲቲዉ ትራፊክ ፖሊስ፣ በትራንስፖርትና ስምሪት እና በፀጥታና ደህንነት ክፍሎች አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን ወደየተመደቡበት ካምፓስ ያለእንግልት በማድረስ ዩኒቨርሲቲውን በሠላም እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

 
(Corporate Communication Directorate)