የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከሚገኙ ዞኖች ለተወጣጡ 26 የጤና ባለሙያዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ  የምክርና ምርመራ አገልግሎት ላይ ከጥቅምት 15-25/2009 ዓ.ም ለ11 ተከታታይ ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ Click here to see participant pictures

 

የስልጠናው ዋና ዓላማ የጤና ባለሙያዎችን ዕውቀትና ክህሎት በማዳበር የተቀዛቀዘው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክርና ምርመራ አገልግሎት በሰፊው እንዲሰጥ ማነቃቃት መሆኑን የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ንጋቱ አካለወልድ ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምንነት፣ መተላለፊያና መከላከያ ዘዴዎች፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምርመራ፣ የጥንዶች የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ምክርና ምርመራ አገልግሎት፣ አዲሱ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ  መመርመሪያ መሣሪያ አጠቃቀም እንዲሁም ለነፍሰ ጡር እናቶችና ለህጻናት የሚሰጥ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምርመራ ላይ ዕውቀትና ክህሎት አግኝተዋል፡፡ በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታልና በአርባ ምንጭ ከተማ ጤና ጣቢያ በመገኘትም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ተመርማሪ መረጃ አመዘጋገብ፣ የኮንዶም አቀማመጥና ሥርጭት፣ የምክክር አገልግሎት አሰጣጥና የአዲሱ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መመርመሪያ መሣሪያ አጠቃቀም በተግባር ምልከታ አድርገዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት የምክር አገልግሎት፣ የናሙና አወሳሰድ፣ የምርመራ አሠራር እና የውጤት አሰጣጥ ላይ በቂ ዕውቀት መጨበጣቸውን ገልፀው ባገኙት ዕውቀት የምክርና ምርመራ አገልግሎቱን በማዘመን ህብረተሰቡን የበለጠ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ዓለሙ ጣሚሶ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረገው ርብርብ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡