የሥነ-ትምህርትና ስነ-ባሕርይ ሳይንስ ትምህርት ቤት በ2009 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን ለተቀላቀሉ አዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት መምህራን ከጥቅምት 21-25 /2009 ዓ.ም ድረስ የማስተማር ስነ-ዘዴ የክህሎት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ Click here to see participant pictures

 

 

ስልጠናው በዋናነት አሳታፊ የማስተማር ዘዴ፣ የመማር ማስተማር ሂደት በክፍል ውስጥ፣ ተከታታይ ምዘናና የዕቅድ አዘገጃጀት እንዲሁም የማስተማር ስነ-ዘዴ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚሉ ርዕሶች ላይ ተሰጥቷል፡፡

አሳታፊ የመማር ማስተማር ስነ-ዘዴን ተጠቅሞ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር፣ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ተማሪዎች ትምህርቱን መከታተላቸውን ማወቅ፣ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተከታታይ ምዘና መስጠትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊተገበር የሚገባ የማስተማር ሥነ -ምግባር በሥልጠናው ተብራርተዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የሁሉም አካላት ድርሻ ቢሆንም የመምህራን ሚና የጎላ መሆኑን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ስልጠናው የተሻለና ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ሰልጣኝ መምህራን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ጠቃሚ ክህሎት እንዳስጨበጣቸውና በመማር ማስተማር ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመወጣት የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው 100 የሀገር ውስጥና 50 የውጭ ሀገር በድምሩ 150 አዲስ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን በሥልጠናው ማጠናቀቂያ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

(Corporate Communication Directorate)