በመከናወን ላይ ባሉና በተጠናቀቁ 172 የምርምር ሥራዎች ላይ ከኅዳር 8-10/2009 ዓ/ም አውደ ጥናት ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እንደገለፁት የዓውደ ጥናቱ ዓላማ የምርምር ሥራዎቹን መገምገም እና ከምሁራን አስተያየቶችን በመውሰድ ጥራታቸውን ማሳደግ ነው፡፡  ምስሎቹን ለማየት እዚሁ ይጫኑ

የአሣ፣ ቡና፣ ቦዬ፣እንሰትና አፕል ምርታማነትና ድህረ ምርት አያያዝ፣የኩልፎ ወንዝ ፕሮጀክት፣የሞሪንጋ ፓርክ ማቋቋም፣ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በኮንሶ ብሄረሰብ፣ የሐመር ስነ-ቃልና ማህበራዊ ፋይዳዎች፣የቋንቋ መምህራን ተከታታይ ምዘና አተገባበር በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በኩልፎ ወንዝ ፕሮጀክት ላይ ሁለት ንዑሳን ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው በአርባ ምንጭ ከተማ የኩልፎ ወንዝን በመግራትና የወንዙን ፍሰት በመቆጣጠር በወንዙ ዙሪያ በሚገኙ ማህበረሰቦች ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የተለያዩ የሃይድሮሊክ መዋቅር ግንባታዎችን ለመሥራት የሚያስችል ነው፡፡ ሌላኛው የወንዙን አካባቢ ለመዝናኛ እና ቱሪስት መስህብነት እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የዲዛይን ሥራ የቀረበበት ነው፡፡ ከቀረቡት ጥናቶች 40 በመቶው የተጠናቀቁ የምርምር ሥራዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 60 በመቶው በመካሄድ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ትኩረት የሃገሪቱን የፖሊሲ አቅጣጫና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ እና በየጊዜው የሚሻሻል መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በግርጫ ደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል፣የስነ-ህይወታዊና ባህላዊ ብዝሃነት ምርምር ማዕከል፣የታዳሽ ሃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል፣ደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከልና የተዘነጉ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምር ማዕከል የምርምር ሥራዎችን በማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡በምርምር ሥራዎች የሚሳተፉ መምህራንን ቁጥር ወደ 45 በመቶ ለማሳደግና ችግር ፈቺ ምርምሮችን 700 ለማድረስ በስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ተካቶ እየተሠራበት እንደሚገኝ ዶክተር ስምዖን አክለው ገልፀዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ዳይሬክተሮች፣ ተመራማሪዎች፣የምርምር አስተባባሪዎች፣የምርምር ማዕከላት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የምርምር ሥራዎቹን ላማሻሻል የሚረዱ ሀሳብና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡