በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ሥር የተከፈተውን የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ የትምህርት ፕሮግራም ለማጠናከር በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ከእንግሊዝ ሀገር ተገዝተው የገቡ መሣሪያዎች አጠቃቀምን አስመልክቶ ለላብራቶሪ አሲስታንቶች እና መምህራን ከህዳር 19- 22/2009 ዓ/ም ለ4 ተከታታይ ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሥልጠናው ዓላማ በትምህርት ክፍሉ ያሉ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር በመታገዝ ብቁ ሆነው እንዲወጡ ማስቻልና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ወንጀልና ወንጀል ነክ ጉዳዮችን መከላከል መሆኑን የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ፕሮግራም አስተባባሪ መ/ር እዮብ ሙሉጌታ ገልፀዋል፡፡

መሣሪያዎቹ በሶፍት ዌር በመታገዝ የሚሠሩና ወንጀሎች በሚፈፀሙበት ጊዜ አሻራን፣ ፈሳሽ ነገሮችን፣ የተጭበረበሩ ዶክመንቶችን፣ የባንክ  ኖቶችን፣ ፓስፖርት፣ የእጅ ፅሁፍ አሻራዎችን፣ ቀለማትንና ያረጁ ወረቀቶች ላይ ያሉ ጽሑፎችን ትክክለኛነት ለመለየት የሚያስችሉ መሆኑን ከእንግሊዝ ፎስተር ኤንድ ፍሪማን ካምፓኒ የመጡት አሰልጣኝ ሚስተር ዳን ፍሪማን በስልጠናው ወቅት ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ኃ/ሚካኤል እንደገለጹት መሳሪያዎቹ በ11 ሚሊየን ብር የተገዙና ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ረገድም ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ መሆኑን ገልፀው መሳሪያዎቹ እንደመጡ ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉም ሊበረታታ የሚገባ ነው፡፡ በተጨማሪም ትምህርት ክፍሉ መሳሪያዎቹን በአግባቡ በመጠቀም ለተማሪዎች በቂ ዕውቀትን እንዲያስተላልፍ አሳስበው በቀጣይ ህብረተሰቡም በመሳሪያዎቹ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ እንደሚመቻች ገልፀዋል፡፡

የአካዳ/ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ስልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለፖሊሶች፣ ለአየር መንገድና ለባንክ ሠራተኞች የሚሰጥ መሆኑንና መሳሪያው ከአካባቢው ማህበረሰብ አልፎ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለአገልግሎት እንዲበቃ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ተጨማሪ መሳሪያዎችን በመግዛትና ማዕከላዊ ላቦራቶሪ በማቋቋም ሌሎች ኮሌጆችና ተቋማት እንዲጠቀሙበት የታሰበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች መሳሪያዎቹን በመጠቀም በቂ የተግባር ልምምድ አድርገው ዕውቀትን እንዲጨብጡና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ለሀገራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡