በቦንኬ ወረዳ ለተቋቋመው የአትሌቲክስ ፕሮጀክት ድጋፍ ተደረገ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት አደራጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍም በ2008 ዓ/ም በቦንኬ ወረዳ ገረሴ ከተማ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ 15 ታዳጊ ወጣቶችን በመመልመል ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ለአትሌቲክስ ፕሮጀክት ቡድኑ ሠልጣኞች አካዳሚው ታህሳስ 8/2009 ዓ/ም ሙሉ ቱታና የልምምድ ማሊያዎችን በማበርከት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል የጫማና ሌሎች የልምምድ ቁሳቁሶች፣ የአሠልጣኞች ሥልጠናና እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ በአካዳሚው የክህሎት ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ በዛብህ አማረ ገልፀዋል፡፡ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች አትሌቶቹ ያሉበትን ደረጃ በመገምገም አፈፃፀማቸው ላይ ክትትል እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፃና ፃሳ በበኩላቸው ዞኑን በሀገራችን አትሌቲክስ ዘርፍ ታዋቂ ከሆኑ አካባቢዎች ተርታ ለማሰለፍ መሰል የአትሌትክስ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ እያካሄደ ያለው የፕሮጀክት ምስረታና ድጋፍ አርዓያነት ያለው ተግባር በመሆኑ በቦንኬ ወረዳ ህዝብና በጽ/ቤታቸው ስም ለዩኒቨርሲቲው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እየተዳከመ የመጣውን የወረዳውን የአትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴ በማገዝ ረገድ ድርሻው የጎላ በመሆኑ ጽ/ቤቱ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በወረዳው ይህንን የፕሮጀክት ስልጠና በመጀመሩ ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት የሰልጣኝ ታዳጊዎች ወላጆች ወረዳው ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለው ግንኙነት በሌሎች ዘርፎችም እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው ከግብ እንዲደርስ የወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤትና ሁሉም የሰልጣኝ ታዳጊዎች ወላጆች የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት ከስልጠናው ባሻገር የግል ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ስፖርተኞቹ በዚህ ረገድ የራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ አበክረዋል፡፡

የሥልጠናውን ሂደትና ተያያዥ ሁኔታዎች በቅርበት የሚከታተሉ ሦስት የወላጅ ኮሚቴዎች ተመርጠዋል፡፡