የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሲምፖዚየም አዘጋጀ

የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ከኢትዮጵያ ሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ማህበር አ/ም/ዩ ጋር በመተባበር ታህሳስ 12 /2009 ዓ/ም ሲምፖዚየም አዘጋጅቷል፡፡

የሲምፖዚየሙ ዓላማ በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ማስተካከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየትና ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ሲወጡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ከሌሎች ምሁራን ተሞክሮዎችን በመቅሰም ግንዛቤያቸውን ማዳበር መሆኑን የትምህርት ክፍሉ ተጠሪ መ/ር ሀብታሙ መለሰ ገልፀዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ የተለያዩ የጥናት ፕሮፖዛሎች ቀርበዋል፡፡ ከውጭ ሀገር የሚገቡ የግንባታ መሣሪያዎችን በማስቀረት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት፣ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪውን ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ መልኩ ማስቀጠል፣ የግንባታ መሣሪያዎች የላቦራቶሪ ፍተሻና የህንፃዎች ጥራት አጠባበቅ ከቀረቡ ፕሮፖዛሎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ሲምፖዚየሙ ተማሪዎች በሥራ ላይ ስለሚገጥሟቸው ችግሮችና በግንባታ ሥራ ወቅት የህንፃውን አቅምና እድሜ የሚቀንሱ እንደ ዝገት፣ የአሠራር ቅደም ተከተሎች፣ የኮንክሪት ጥራት፣ የዲዛይን ሁኔታና የህንፃዎች መፈረካከስን አስመልክቶ መደረግ ስለሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲያውቁና የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ የሚረዳ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የ5ኛ ዓመት ሲቪል ምህንድስና ተማሪና የኢትዮጵያ ሲቪል ምህንድስና ተማሪዎች ማህበር አ/ም/ዩ ሎካል ዩኒት ፕሬዝደንት ተማሪ ሙሉቀን ነጋው ገልጿል፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ አሲስታንት ፕሮፌሰር ናቺሙቱ ሰብራማኒ ሲምፖዚየሙ በተለይም የ4ኛ ዓመት ተማሪዎች በግንባታ ሥራ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ይዘው ለተግባር ልምምድ እንዲወጡና ከመሃንዲሶች ተጨማሪ ዕውቀትን እንዲቀስሙ ታስቦ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ተማሪዎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንን በመጋበዝ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡