የዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደህንነት ጽ/ቤት ለአባላቱ ሥልጠና ሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደህንነት ጽ/ቤት ከታህሳስ 11/2009 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 20 ቀናት በሁለት ዙሮች ለክፍሉ ሠራተኞች የቲዮሪና የተግባር ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ወታደራዊ ሠልፍ፣ የመሣሪያ አፈታትና አገጣጠም፣ ዒላማ እንዲሁም የዲሲፕሊን ቅጣትና ዓይነቶች በሥልጠናው የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሥልጠናው ዓላማ የፀጥታና ደህንነት አባላት በወታደራዊ ቁመናና አስተሳሰብ ብቁ እንዲሆኑ፣ መመሪያና ደንቦችን አውቀው እንዲሠሩ ብሎም በወንጀል መከላከልና በህገ መንግስት ድንጋጌዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ማገዝ መሆኑን የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሻለቃ አበበ አማረ ገልፀዋል፡፡

የአስተዳደር ጉ/ም ፕሬዝደንት አቶ በኃይሉ መርደክዮስ እንደገለፁት ፀጥታን ማስከበር የፀጥታና ደህንነት አባላት ድርሻ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡን የተጠናከረ ድጋፍ የሚጠይቅ ነው፡፡ አባላቱ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ በወንጀል መከላከል፣ መረጃዎችን በማሰባሰብና በወንጀለኝነት የተጠረጠሩ ሰዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር በማዋል የተፋጠነ የውሳኔ ሂደት እንዲኖር ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ትምህርትና ሥልጠና ኃላፊ ም/ኢንስፔክተር  ዘመነ ሽጉጥ እንደገለፁት ሥልጠናው የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ ግንዛቤን የሚያሳድግ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው  የሚገጥሙ ማናቸውንም ችግሮች በሠለጠነና ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ይረዳል፡፡

ሠልጣኞች በአስተያየቶቻቸው ሥልጠናው ያለንበትን ደረጃ እንድንፈትሽ፣ አቅማችንን እንድናመጣጥንና የሚገጥሙ ችግሮችን በሰከነ መንፈስ እንድንፈታ በቂ ዕውቀትና ክህሎት አስጨብጦናል ብለዋል፡፡