በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት አምስተኛው ዙር የቱሪዝም ሳምንት "RESPONSIBLE TOURISM AND HOSPITALITY EMPLOYMENT FOR THE GREATER GOOD" በሚል መሪ ቃል ከታህሳስ 18-23/2009 ዓ.ም በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በድምቀት ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በዓሉን አስመልክቶ በጫሞ ካምፓስ የቱሪዝም ፓርክ በመከለል የሀገር በቀል ችግኞች ተከላ፣ የፓናል ውይይት፣ የሴቶች እግር ኳስ ግጥሚያ፣ ሚኒ ማራቶን፣ የሰርከስ ትርኢት፣ በሁለቱም ፆታዎች የባህላዊ ውዝዋዜና የዘመናዊ ሙዚቃ የድምፅ ውድድሮች እንዲሁም የተመልካችን ቀልብ የሳበ የቁንጅና ውድድር ተካሂዷል፡፡ በቁንጅና ውድድር ከ1ኛ - 3ኛ ለወጡ ከ1000-1500 ብር እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች በየደረጃቸው ከ100-500 ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ዋኘው እሸቴ እንደገለፁት የቱሪዝም ሳምንት መከበሩ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲያሳዩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርና ትምህርት ክፍሉን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የጎላ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው፡፡

ጋሞ ጎፋ ዞን በርካታ የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻ ሥፍራዎች ያሉት በመሆኑ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ተቋማትና ከሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የኮሌጁ ዲን ዶ/ር መልካሙ ማዳ ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝም ሳምንት መከበሩም መልካም ገፅታ ከመገንባት ጎን ለጎን ዞኑንና የቱሪስት መስህቦቹን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ዕድል የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ መ/ር ጋሻው ጌታሁንና መ/ር ደራራ ከተማ በፓናል ውይይቱ ላይ ባቀረቡት ሰነድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ሰፊ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሐይማኖታዊ ቅርሶችና ጥንታዊ ቅሪተ አካሎች መገኛ ብትሆንም ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ዕድገት አለማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህም በዘርፉ ያለውን አቅም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ገበያ በማስተዋወቅ እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ኃይል በማሰማራትና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ለሀገራዊ ፋይዳው መረባረብ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የደቡብ ክልል ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ/ቢሮ ተወካይ አቶ ለማ መሰለ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የቱሪዝም ዘርፍ ማበርከት የሚገባውን ያህል ጥቅም እያስገኘ አይደለም፡፡ ስለሆነም የተማረውንና የሰለጠነውን የሰው ኃይል በሣይንሣዊና በተደራጀ መልኩ በማዋቀር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች በበኩላቸው በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑና በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚመለከታቸው አካላት ከጎናቸው እንዲቆሙ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ሰነዱን ተከትሎ የተደረገው የጋራ ውይይትና የታዳሚዎች አስተያየት የጋራ ግንዛቤውን ያዳበረና የሰነዱን ጭብጥ ያጎለበተ ነበር፡፡

በፕሮግራሙ የዞን ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ መምሪያና የክልሉ ባ/ቱ/መ/ኮ/ጉ ቢሮ ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች ታድመዋል፡፡