በሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም በምግብ ንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ከሁሉም ካምፓሶች ለተወጣጡ ከ25 በላይ የካፍቴሪያና የጥገና ክፍል ሠራተኞች በሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም የተማሪዎች ምግብ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ታህሳስ 18/2009 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የሥልጠናው ዓላማ ሠራተኞች የሥራ አካባቢያቸውን ተስማሚ በማድረግ እንዲሁም ከበሽታ አመንጪ ተህዋሲያን  የነፃ የምግብ አገልግሎት በመስጠት የተማሪዎችን ብሎም የራሳቸውንና የሌሎች ሠራተኞችን ጤንነት እንዲጠብቁ ማድረግ መሆኑን የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ዓለሙ ገልፀዋል፡፡

ለሴቶች፣ ለነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ለወጣት ሠራተኞች ከባድና ለጤና ጎጂ ሥራዎችን በተመለከተ የተደነገጉ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ  ህጎችና መመሪያዎች፣ በሥራ አካባቢ የሚከሰቱ የጤና እክሎች፣ ምግብ ወለድና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችና ጥንቃቄዎች እንዲሁም የምግብ ቤት ሠራተኞች የግል ንጽህና አጠባበቅ ላይ ሠልጣኞች ግንዛቤ  አግኝተዋል፡፡

ለነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ ሴቶች የፀረ-ተባይና ፀረ-አረም ውህዶችን መበጥበጥ፣ መሙላት፣ ማሸግና መርጨት እንዲሁም በማንኛውም የጉድጓድ ወይም የዋሻ ቁፋሮ መሰማራት የተከለከለ መሆኑ በሥልጠናው ተገልጿል፡፡

የተበከለ አየር፣ አቧራ፣ ጭጋግ፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ ጽዳት የጎደለው የሥራ ቦታ፣ ከአቅም በታችና በላይ መሥራት፣ የተበታተነ የሥራ ይዘት እና የዕቃ ማንሻ ማሽን አጠቃቀም ችግሮች በሠራተኞች ላይ የጤና መታወክ፣ ምቾት ማጣትና የሥራ ብቃት መቀነስን እንደሚያስከትሉ የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የአካባቢ ደህንነትና ጤንነት ስራ ክፍል አስተባባሪ አቶ አያልቅበት ቦዳ ገልፀዋል፡፡ በምህንድስና፣ አስተዳደራዊ እና የግል አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ምቹና ጤናማ የሥራ አካባቢ መፍጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ሥልጠናው አገልግሎት አሰጣጣችን ዘመናዊ፣ ንጽህናውን የጠበቀና ደህንነታችን ላይ አደጋ የማያስከትል እንዲሆን አቅም የሚፈጥርልን ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የሁሉም ካምፓሶች የካፍቴሪያና የጥገና ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡