በተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከሁሉ ዓቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ለመስተንግዶና ወጥ ቤት ባለሙያዎች እንጀራ ጋጋሪዎች እና የምግብ ጥራት ተቆጣጣሪዎች በምግብ አያያዝና በንፅህና አጠባበቅ ላይ ታኅሣሥ 25/2009 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሁሉ ዓቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የሥራ አካባቢ ደህንነት ባለሙያ አቶ ዘላለም ንጋቱ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ የተማሪዎች አገልግሎት ሠራተኞች በንፅህና አጠባበቅ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማዳበር የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራታቸውን የተሻለ ማድረግ ነው፡፡

ምግብ ወለድ ህመም፣ የምግብ ቤት ሠራተኞች የግል ንፅህና አጠባበቅ እና የምግብ አሠራር ንፅህና በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርዕሶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ሠልጣኞች ምግብ ሲያዘጋጁና ሲያቀርቡ አፍንጫን ከመጎርጎር፣ ፀጉርን በእጅ ከመነካካትና መሰል ልማዶች በመቆጠብ ፅዳት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ዘላለም ገልፀዋል፡፡

በቂ የሠራተኞች መፀዳጃና ሻወር ቤት ያለመኖር፣ ለፅዳት የሚረዱ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት፣ የሥራ ጫናዎች መደራረብ፣ በቂ ረፍት ያለማድረግ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ያለመኖርና መሰል ምክንያቶች ለንፅህና አጠባበቁ እንቅፋቶች እንደሆኑ ሠልጣኞች በአስተያየታቸው ገልፀዋል፡፡ ሥልጠናው የዕለት ከዕለት ሥራቸውን የተሻለ ለማድረግና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡