የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በጋሞ ጎፋ ዞን የአርባ ምንጭ እና የሣውላ 2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤቶች የልህቀት ማዕከልና ሞዴል ት/ቤት ሆነው ለትምህርት ጥራት አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ታህሳስ 25/2009 ዓ/ም የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

የውይይት መድረኩ ቀደም ሲል የተከናወነውን የዳሰሳ ጥናት መነሻ በማድረግ የተመረጡ ት/ቤቶችን ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሸጋገር በሚደረገው ሂደት የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚረዳ መሆኑን የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ገልፀዋል፡፡

የተመረጡት ትቤቶች በጋሞ ጎፋ ውስጥ ቀዳሚና ብዙዎች ተምረው የወጡበት ቢሆንም ከቴክኖሎጂውና ከህዝብ ቁጥር ጋር አብረው ያላደጉና በ2ቱም ት/ቤቶች በርካታ ተመሳሳይ ክፍተቶች የሚስተዋሉባቸው በመሆናቸው በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማስተካከል የሚያደርገውን ጥረት በማበረታታት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በሙሉ ኃይል ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ትምህርት ቤቶቹ ያሉበትን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ ዝርዝር የዳሰሳ ጥናት የቀረበ ሲሆን የትምህት ጥራትን እውን ከማድረግ አንፃር ት/ቤቶቹን ወደ ልህቀት ማዕከልነት የማሳደግ አስፈላጊነትና ቀጣይ የአተገባበር እቅዶችን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል፡፡

ለትግበራ ሂደቱም ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ 14 ኮሚቴዎች የተዋቀሩ ሲሆን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሰቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሰብሳቢ፣ ከዞን ትምህርት መምሪያ ፀሐፊ እንዲሁም ከአ/ምንጭና ከሳውላ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤቶች የትምህርት ጥራትና የልማት ዕቅድ ባለሙያ፣ ከአ/ምንጭና ሳውላ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤቶች፣ የሁለቱ ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮችና የዳሰሳ ጥናቱን ያካሄዱ የስነ- ትምህርት ባለሙያዎች በአባልነት ተመርጠዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው እንደገለጹት እያንዳንዱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ አንድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅበት የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የሚገኙ የ2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶችን ለመደገፍ ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በያዝነው በጀት ዓመት ከዞኑ ስፋት አንፃር ሁለት ትምህርት ቤቶችን ብቁ ተማሪዎች የሚፈልቁበትና ሌሎች ት/ቤቶች ልምድ የሚቀስሙበት የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ያቀደ ሲሆን ትምህርት ቤቶቹ ሁለት መሆናቸው በጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር የዞኑ ትምህርት መምሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከዩኒቨርሲቲው ጋር መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማህ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ በበኩላቸው ት/ቤቶቹ ያሉባቸውን በርካታ ችግሮች በመፍታትና ዕቅድ አዘጋጅቶ በተሻለ ሁኔታ በማደራጀት በዙሪያቸው ላሉ ት/ቤቶች የልህቀት ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ት/ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ የልህቀት ማዕከልነት ደረጃን አሟልተው የላቁና የበቁ ተማሪዎችን በማፍራት በትምህርት ጥራት ላይ የተያዘው ሀገራዊ ራዕይ እውን እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የዞኑ አስተዳደር፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸው ክፍሎች ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመቆም በትምህርት ቤቶቹ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በጋራ ለማከናወን የድርሻቸውን መወጣትና የተጀመረውን ሥራ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የዞን ትምህርት መምሪያ፣ የአርባ ምንጭ እና የሣውላ ከተሞች ትምህርት ጽ/ቤቶች ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡