የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከደ/ብ/ብ/ህ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ከክልሉ ዞኖች ለተወጣጡ 18 የጤና ባለሙያዎች በማህጸን ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ከታህሳስ 17-25/2009 ዓ.ም ለአስር ተከታታይ ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ 

የሥልጠናው ዓላማ በማህፀን ጫፍ ካንሰር የተያዙ ህሙማንን በምርመራ በመለየት እና በቅድመ ካንሰርና በካንሰር ደረጃ ለሚገኙ ህሙማን ህክምና በመስጠት ጤናማና አምራች እናቶችን መፍጠር እንዲሁም በማህፀን ጫፍ ካንሰር ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ነፍስ መታደግ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ም/ኃላፊና የበሽታ መከላከል ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አቅናው ካውዛ ተናግረዋል፡፡

የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ መንስኤዎች፣ የመከላከያና የምርመራ ዘዴዎች፣ የመመርመሪያ መሳሪያ አጠቃቀም፣ በበሽታው ለተጠቁ ህሙማን የምክር አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ሀገራዊና ክልላዊ የማህፀን ጫፍ ካንሰር መረጃዎች በስልጠናው ተዳሰዋል፡፡

በሥልጠናው እንደተገለጸው የማህጸን ጫፍ ካንሰር ዕድሜያቸው ከ15-45 የሆኑ ሴቶችን የሚያጠቃና 70 በመቶ ገዳይ የሆነ በሽታ ሲሆን ለበሽታው መከሰት ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (Human papilloma virus) የተባለና በግብረ-ሥጋ ግንኙነት አማካይነት የሚተላለፍ ህዋስ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ በለጋ ዕድሜ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት መጀመር፣ ከብዙ ወንዶች ጋር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ወይም ከብዙ ሴቶች ጋር ግንኙነት ካለዉ ወንድ ጋር ጥንቃቄ የጎደለዉ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ፣ በሌሎች የአባላዘር ህመሞች መያዝ፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የበሽታ መከላከል አቅም ደካማ መሆን እና ሲጋራ ማጨስ ለበሽታው አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በሽታውን ለመከላከል ከሚረዱ መፍትሔዎች መካከል ንጽህናን መጠበቅ፣ በአንድ መወሰን፣ ዕድሜ ከ25 ዓመት በላይ ከሆነ በየዓመቱ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣ እራስን ከአባላዘር በሽታ መከላከል፣ ሲጋራ እና የመሳሰሉትን ሱስ አስያዥ ዕጾች አለመጠቀም እና በወሲባዊ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም ይጠቀሳሉ፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በማህፀን ጫፍ ካንሰር ላይ ያላቸውን የግንዛቤ ውስንነት በማስቀረት በቅድመ ካንሰር ደረጃ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲችሉ፣ በምርመራ ወቅት የማህጸን ጫፍ ካንሰርን በቀላሉ እንዲለዩና ህክምናውን በአግባቡ እንዲሰጡ የሚያስችል አቅም የገነባላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡