አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2009 የትምህርት ዘመን የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ

የዩኒቨርሲቲው የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ካውንስል፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የት/ቤት ኃላፊዎች፣ የትምህርት ክፍል ተጠሪዎችና አስተባባሪዎች እንዲሁም ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች በተገኙበት ጥር 9/2009 ዓ/ም ቀርቧል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የግምገማው ዓላማ በግማሽ ዓመቱ የታቀዱ ተግባራት በአግባቡ መከናወናቸውን በመገምገም ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው መስኮች በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደት ማስፈን መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡

በሪፖርቱ እንደተገለፀው በርካታ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች መጀመራቸው፣ የተማሪ ቅበላ አቅም ማደጉ፣ የቤተ- መፅሐፍት አጠቃቀም ወደ ዲጂታል ሥርዓት መቀየሩ፣ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ባሉ አጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የነፃ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው፣ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ ሴት ተማሪዎችና በሥራቸው የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱ፣ የመፅሐፍ እጥረትን ለመቅረፍ የበርካታ መፅሐፍት ግዥ መፈፀሙ፣ በ2008 የት/ት ዘመን ኤፍ ኤክስ ያመጡ ተማሪዎች በድጋሚ ፈተና አጥጋቢ ውጤት እንዲያመጡ መደረጉ፣ የ 1 ለ 5 አደረጃጀት ተጠናክሮ በመተግበር ላይ መሆኑ እንዲሁም የኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የሥነ-ተዋልዶ ጤና እና የህይወት ክህሎት ሥልጠና ለሁሉም የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች መሰጠቱ በመማር ማስተማር ዘርፍ የተመዘገቡ ጠንካራ አፈፃፀሞች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በአስተዳደር ዘርፍ ከተመዘገቡ ስኬታማ ተግባራት መካከል የዲሲፕሊን ኮሚቴ በየኮሌጁ መቋቋሙ፣ ስማርት አይዲ ካርድ መዘጋጀቱ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት መደረጉ እንዲሁም ሣምንታዊ የሥራ ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ተጠናክሮ መካሄዱ ተጠቅሰዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ጆርናሎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አደረጃጀቶች ክለሳ መሠራቱ፣ የምርምር ውጤቶች ዕውቅና ባላቸው ጆርናሎች እንዲታተሙ መደረጉ፣ ከእንጦጦ ህዋ ምልከታ ጣቢያ ጋር በመተባበር በጉጌ ተራራ ለሚቋቋመው የህዋ ምልከታ ጣቢያ የቅድመ አዋጭነት ጥናት የመጀመሪያ ሪፖርት መጠናቀቁ፣ የግርጫ የምርምር ማዕከል ጠንካራ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑ፣ ዘላቂ የዕውቀት ማዕከል ለማቋቋም ከግሎባል ማፕ ኤይድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ከተከናነወኑ ጠንካራ አፈፃፀሞች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በታዳሽ ኃይል የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ለ1ኛና 2ኛ ደረጃ የገጠር ት/ቤቶች ሶላር ሲስተም ለመዘርጋት ቤልጂየም ከሚገኘው ኢነርጂ አሲስታንት ቡድን ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተወጣጡ 450 ከ7ኛ - 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የላቦራቶሪ ሥልጠና እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ነፃ የህግ አገልገሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በአንፃሩ የኦሞቲክ ቋንቋዎች ምርምር ማዕከል ለማቋቋም ታቅዶ አለመፈፀሙ፣ የዩኒቨርሲቲውን ሴት ሠራተኞች ለ2ኛ ዲግሪ ትምህርት ለማብቃት ታቅዶ አለመከናወኑ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ተሳትፎ ካለፈው ዓመት የተሻለ ቢሆንም የታቀደውን ያህል አለመፈፀሙ፣ መጠነ ማቋረጥ በሴት ተማሪዎች ላይ ከፍ ማለቱ፣ የቀድሞ ተመራቂ ተማሪዎች ማኅበር/አልሙኒ/ አለመጠናከሩ፣ በመካከለኛና ከፍተኛ አመራር ቦታዎች የሴቶች ተሳትፎ አለማደግ፣ የመምህራን በተለያዩ ምክንያቶች ዩኒቨርሲቲውን መልቀቅና በአንዳንድ የትምህርት መስኮች በቂ መምህራንን መቅጠር አለመቻል፣ የተሽከርካሪ እጥረት፣ የግንባታዎች መጓተት እንዲሁም የተማሪ ኮምፒውተር እና የተማሪ መ/ር ጥምርታ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሪፖርቱን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ መልካም አፈፃፀሞችን ይበልጥ በማጠናከርና ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው የሥራ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ ዶ/ር ዳምጠው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ የታቀዱ ተግባራት ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑና በመማር ማስተማር ሂደት ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባልም ብለዋል፡፡