24ኛው የአካል ጉዳተኞች ቀን በድምቀት ተከበረ

‹‹ለመጪው ዘመን ብሩህነት አካል ጉዳተኞችን በማካተት አሥራ ሰባቱን ዘላቂ የልማት ግቦች እናሳካ›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ 24ኛውን የአካል ጉዳተኞች ቀን ዩኒቨርሲቲው ኅዳር 25/2009 ዓ.ም በድምቀት አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ዩኒቨርሲቲው ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እያደረገ ባለው ድጋፍ ላይ ውይይት በማድረግና አፈፃፀሙን በመገምገም ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓት ለመሰብሰብ ታስቦ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጳውሎስ ታደሰ ገልፀዋል፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት አካል ጉዳተኞችን፣ ሴቶችንና ኋላ ቀር አካባቢዎችን በልማት፣ በጤና እና በትምህርት ዕድል እኩል ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሉ አፈፃፀሞች እያሳየች ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ያካተተ ዕቅድ አዘጋጅቶ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን በማመቻቸት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እያደረገ ይገኛል፡፡

የመማሪያና ማደሪያ ህንፃዎች ግንባታ፣ የኮምፒውተር ማዕከል፣ የመጸዳጃና ሻወር አገልግሎቶች፣ የካፍቴሪያ አገልግሎት፣  የማጠናከሪያ ትምህርት እና የማበረታቻ ሽልማቶች ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ከአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በየዘርፉ ድክመቶች የሚስተዋልባቸው አፈፃፀሞች በቀጣይ ትኩረት እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡

አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገው ድጋፍ ለትምህርታቸው ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀው በትምህርታቸው የላቀ ውጤት በማምጣት ለሀገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የተማሪዎች ኅብረትና የሠላም ፎረም አመራሮች እንዲሁም የሁሉም ካምፓሶች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን አርባ ምንጭ አዞ እርባታንና አርባ ምንጮችን ጎብኝተዋል፡፡